ትዊተር የትራምፕን አካውንት በቋሚነት አገደ
ፕሬዝዳንቱ በባይደን በዓለ ሲመት ላይ አልታደምም ማለታቸው ፣ ደጋፊዎቻቸው ዝግጅቱን እንዲረብሹ መልዕክት እንደማስተላለፍ ነው ተብሏል
ፕሬዝዳንት ትራምፕ የትዊተር ገጻቸውን ለተጨማሪ አመጽ መቀስቀሻነት እንዳይጠቀሙ በሚል ነው የታገደው
ትዊተር የተሰናባቹን ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ የትዊተር ገጽ በቋሚነት ማገዱን አስታወቀ፡፡
ትዊተር ይህንን ውሳኔ ያስተላለፈው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ያሰራጩትን ጽሑፍ ከመረመረ በኋላ መሆኑን ሲኤንኤን ዘግቧል፡፡ @realDonaldTrump የሚለው የፕሬዝዳንቱ ገጽ ፣ ለተጨማሪ የአመጽ ቅስቀሳ ተጠቅመውበት ሌላ ጉዳት እንዳያደርሱ በሚል ነው የተዘጋው፡፡
ፕሬዝዳንት ትራምፕ ያቀረቡትን ጥሪ ተከትሎ ፣ ባለፈው ረቡዕ ደጋፊዎቻቸው የአሜሪካ መንግሥት መቀመጫ የሆነውን ካፒቶል ሂልን ሰብረውበመግባት የኮንግረሱን ስብሰባ ከማስተጓጎላቸው በተጨማሪ አንድ ፖሊስን ጨምሮ 5 ሰዎች እንዲሞቱ ምክንያት ሆነዋል፡፡ ይህን ተከትሎም ፕሬዝዳንቱ ሰልፈኞቹን በማድነቅ የጻፏቸው ጽሁፎች ትዊተርን ጨምሮ በተለያዩ የማህበራዊ ትስስር ገጾች ተሰርዘዋል፤ ፕሬዝዳንቱም ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸው በጊዜያዊት ታግደው ነበር፡፡
በአሜሪካ አንዳንድ ሕግ አውጪዎችና ታዋቂ ግለሰቦች የትራምፕ ገጽ እዲታገድ ከዚህ በፊት በተደጋጋሚ ሲጠይቁ እንደነበር ይታወሳል፡፡
የቀድሞዋ ቀዳማዊት እመቤት ሚሼል ኦባማ ባሳላፍነው ሐሙስ የሲሊኮን ቫሊ ግዙፍ ኩባንያዎች (ፌስቡክና የመሳሰሉት) የትራምፕን ጭካኔ የተሞላበት ባህሪ ሊያስቀቆሙ እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡
ትራምፕ እ.አ.አ ጥር 20 ላይ ሕጋዊ የሥልጣን ሽግግር እንደሚኖር ቢገልጹም በባይደን በዓለ ሲመት ላይ እንደማይገኙ ገልጸዋል፡፡
ትራምፕ የትዊተር ገጻቸው ከመዘጋቱ በፊት “ለጠየቃችሁኝ ሁሉ ፣ ጥር 20 በሚኖረው በዓለ ሲመት ላይ አልገኝም” ብለው ጽፈዋል፡፡ ይህ ጽሁፋቸው አንድም የምርጫው ውጤት ትክክል አለመሆኑን ሁለትም እርሳቸው ስለማይገኙበት በዓለ ሲመቱ ላይ ደጋፊዎቻቸው አመጽ እንዲያስነሱ መልዕክት ለማስተላለፍ ሊሆን እንደሚችል ትዊተር ግምቱን አስቀምጧል፡፡ ይህም አካውንታቸው (የትዊተር ገጻቸው) ለመዘጋቱ አንዱ ምክንያት ነው፡፡
የአሜሪካ ኮንግረስ አባላት በሀገሪቱ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ለጆ ባይደን አሸናፊነት ማረጋገጫ ለመስጠት ስብሰባ ላይ እያሉ የትራምፕ ደጋፊዎች ወደ ግቢው ገብተው አመጽ ማስነሳታቸውን ተከትሎ በትራምፕ ላይ ዓለም አቀፍ ውግዘት እየደረሰባቸው ነው፡፡