ከ1 ሚሊየን በአንዷ የሚፈጠር አስገራሚ ክስተት - በሁለት ማህጸን መጸነስ
ሁለት ማህጸን ያላት አሜሪካዊቷ የ33 አመት እናት በሁለቱም ጸንሳ መውለጃዋን እየተጠባበቀች ነው
ከ1 ሺህ ሴቶች ሶስቱ ሁለት ማህጸን ኖሯቸው ሊፈጠሩ እንደሚችሉ ጥናቶች ያሳያሉ
በአሜሪካ አንዲት እናት በሁለት ማህጸኖቿ መጸነሷ አነጋጋሪ ሆኗል።
በአላባማ ነዋሪ የሆነችው ኬስሊ ሃቸር ከ17 አመቷ ጀምሮ ሁለት ማህጸን እንዳላት ብታውቅም በሁለቱም ማህጸኖቿ መጸነሷ እንዳስደነገጣት ትናገራለች።
“ለባለቤቴ ካሌብ ስነግረው እየዋሸሽኝ ነው” አለኝ የምትለው ሃቸር በግንቦት ወር ነው በሁለቱም ማህጸኖቿ መጸነሷ በአልትራሳውንድ የታየው።
በሁለቱም ማህጸን ማርገዝ ማለት በቀላሉ ሁለት የተለያየ እርግዝና ተከስቷል እንደማለት ነው የሚሉት የሃቸርን እርግዝና የሚከታተሉት ዶክተር ሪቻርድ ዴቪስ፥ በዚህም ጽንሶቹን መንትያ ማለት እንደሚያስቸግር ይናገራሉ።
እንደ ሃቸር ሁለት ማህጸን ኖሯቸው ሊፈጠሩ የሚችሉት ከ1 ሺህ ሴቶች ሶስቱ ብቻ ናቸው።
በሁለቱም ማህጸን የመጸነስ እድሉም ከ1 ሚሊየን ሴቶች በአንደኛዋ ይሳካል ተብሎ እንደመታመኑም የሃቸር ጽንስ መነጋገሪያ መሆኑ አይገርምም ይላል ኤንቢሲ ኒውስ በዘገባው።
በሁለት ማህጸን የተጸነሱት የሃቸር ሴት ልጆች በገና በዓል ሰሞን ይህቺን ምድር በለቅሶ ይቀላቀላሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ጽንሶቹ በመልካም ጤንነት ላይ መሆናቸውን የሚናገሩት ዶክተር ዴቪስ “እህትማማቾቹ” በስአታት ወይም ቀናት ልዩነት ሊወለዱ እንደሚችሉና በእናትየዋ ላይም የተለያየ የጤና እክል ሊያመጣባት እንደሚችል ገልጸዋል።
በየሳምንቱ በአልትራሳውንድ በተለያየ ማህጸን ውስጥ ያሉ ልጆቿን የምትመለከተው እናት ጭንቀት ውስጥ እንዳትገባም በባለሙያዎች ተገቢው እገዛ እየተደረገላት ነው ተብሏል።
የሶስት ልጆች እናቷ ኬስሊ ሃቸር የቤተሰቡን ቁጥር ወደ ሰባት የሚያሳድጉት ሁለት ግን መንታ የማይሰኙ ልጆች የመጨረሻችን ይሆናሉ ብላለች።