69 ልጆችን የወለደች ሩስያዊ እናት በድንቃ ድንቅ መዝገብ መስፈሯን ያውቃሉ?
በማሊም በአንድ ጊዜ ዘጠኝ ህጻናትን የወለደች እናት በመዝገቡ ላይ ስሟን አስፍራለች
15 ጊዜ ሶስት ህጻናትን የተገላገለችው ጣሊያናዊም በምድራችን ከታዩ 10 አስደናቂ ነፍሰጡሮች መካከል ትካተታለች።
እርግዝና ለማንኛውም ቤተሰብ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ጉዳይ ነው።
ወላጆች ለሚወለዱት ህጻናት ስም ከማውጣትና ቤትን ከማስጌጥ አንስቶ ለአዲሱ ቤተሰቡን ለሚቀላቀለው ህጻን ተገቢው ዝግጅት ይደረጋል።
ነገር ግን ያልተጠበቀው ተከስቶ ወላጆችን ብሎም አለምን የሚያስደምም ዜና ይሰማል።
በአለም ድንቃ ድንቅ መዝገብ የሰፈሩ 10 የተለዩ ነፍሰጡሮች መርጃም ይህን ያሳያል።
1 ካናዳዊቷ አና ቤትስ በፈረንጆቹ 1879 በአለም ድንቃድንቅ መዝገብ የሰፈረ ረጅም ልጅ ወልዳለች። ቤትስ 71 ነጥብ 12 ሴንቲሜትር የሚረዝም እና 10 ኪሎግራም የሚመዝን ልጅን ብትወልድም እድሜው 11 ስአታትን ማለፍ አልቻለም።
2 በተቃራኒው የአለማችን ትንሿ ህጻን (24 ሴንቲሜትር የምትረዝምና ክብደቷ 320 ግራም የሆነች) በአሜሪካ ሚኒሶታ ሚኒያፖሊስ በ2002 ተወልዳለች።
ኒሳ ጁዋሬዝ የተባለችው ትንሿ ህጻን ከመወለጃ ጊዜዋ 108 ቀናት አስቀድማ መወለዷ በሆስፒታል አምስት ወራትን እንድትቆይ አድርጓታል።
3 69 ህጻናትን የወለደች ሩስያዊ
በሩስያ ሹያ በተባላ አካባቢ በ18ኛው ክፍለ ዘመን የፊዮዶር ቫሲልየቭ ባለቤት በህይወት ዘመኗ 69 ልጆችን በመውለድ አሁንም ድረስ በአለም ድንቃድንቅ መዝገብ ስሟ እንደሰፈረ ነው። 16 መንታ፣ ሰባት ጊዜ ሶስት እና አራት ጊዜ አራት ህጻናትን በመውለድ ክብረወሰን ሰባብራለች።
4 በእናቱ ማህጸን 21 ሳምንታት ብቻ የቆየው ኩርቲስ ሚንስ ያለጊዜው ተወልዶ ያደገ እድለኛ ህጻን ነው። ኩርቲስ በ2020 ሲወለድ (420 ግራም ይመዝን ነበር) በህይወት የመቆየት እድሉ 1 በመቶ ብቻ ነው ተብሎ ነበር። ነገር ግን በ2022 ሁለተኛ አመት ልደቱ ተከብሮለታል።
5 ያለጊዜያቸው ተወልደው በህይወት የቆዩ መንትያዎች ደግሞ በአሜሪካ በ2018 የተወለዱት ኬሊ እና ካምብሪ ኢዎልዶት ናቸው። በ22 ሳምንት የማህጸን ቆይታቸው የተወለዱት መንትያዎች 490 እና 379 ግራም ይመዝኑ ነበር።
6 አሜሪካዊቷ ሌስሊ ብራውን ለአመታት የመጸነስ ችግር ነበረባት። እናም አይ ቪ ኤፍ በተሰኘ ዘመናዊ መንገድ የመጀመሪያ ልጇን አግኝታለች። የሌስሊ የዘር እንቁላል ከባሏ ስፐርም ጋር በላብራቶሪ ወደ ጽንስነት ተለውጦ ወደ ማህጸኗ ገብቶ ልዊዝ ብራውን የተሰኘች ህጻን በ1977 ወልዳለች። በዚህ ፈር ቀዳጅ ቴክኖሎጂ እስካሁን 1 ሚሊየን ህጻናት የተወለዱ ሲሆን የመጀመሪያዋ ሌስሊ ብራውን አሁን 45 አመቷ ነው፤ ሁለት ልጆችንም ወልዳለች።
7 በማሊ ዘጠኝ ህጻናትን በአንዴ የወለደችው እንስት የቤተሰቡን ቁጥር 11 አድርሳዋለች። ሃሊማ ሲሴ በ2021 ነው በሞሮኮ ልጆቿን የወለደችው። ከ19 ወራት የሞሮኮ ቆይታዋ በኋላም ወደ ሀገሯ ተመልሳለች።
8 ጣሊያናዊቷ ማዳሌና ግራናታ ደግሞ 15 ጊዜ ሶስት ህጻናትን በመውለድ በድንቃድንቅ መዝገቡ ላይ ሰፍራለች። 45 ልጆችን የወለደችው ግራናታ በ1886 ህይወቷ ማለፉ ከመነገሩ ውጭ ስለ እርግዝናዋ የተብራራ መርጃ የለም።
በአይ ቪ ኤፍ ህክምና ለ30 አመታት በቤተሙከራ የቆየው ጽንስ ለወላጆች መንታ ልጆችን ሰጥቷል። እንግሊዛውያኑ ሪቸል እና ፊሊፕ ራይድወይ፥ ሊዲያ እና ቲሞቲ የተባሉ ልጆችን በ2022 ጥቅምት ወር ላይ አግኝተዋል። የአለም ድንቃድንቅ መዝገብም በአስደናቂ ፍጥረትነታቸው መዝግቧቸዋል።
10 ስፔናዊቷ ማሪያ ዴል ካርሜን በ67 አመቷ መንታ ሕጻናትን በ2006 በባርሴሎና ሳንት ፓኦ ሆስፒታል ወልዳለች። ማሪያ በስፔን የተከለከለችውን የአይ ቪ ኤፍ ህክምና (በላብራቶሪ የመጸነስ ሂደት) ወደ አሜሪካ በማቅናት አግኝታለች።