ሩሲያ በማህጸን ኪራይ የተወለዱ ህጻናት ከሀገር እንዳይወጡ የሚከለክል ህግ አወጣች
ከሩሲያ እናቶች የተወለዱ ከ45 ሺህ በላይ ህጻናት ወደ ውጪ ሀገራት መወሰዳቸው ተገልጿል
ሩሲያ የማህጸን ኪራይን የሚፈቅድ ህግ ያላት ቢሆንም ድርጊቱ በሀይማኖት አባቶች ተቃውሞ ገጥሞታል
ሩሲያ በማህጸን ኪራይ የተወለዱ ህጻናት ከሀገር እንዳይወጡ የሚከለክል ህግ አወጣች።
የሩሲያ ህግ አውጪ ምክር ቤት ወይም ዱማ የሩሲያዊያን እናቶች ከውጭ ሀገራት ዜጎች ጋር በሚደረግ ስምምነት የማህጸን ኪራይ አገልግሎትን የሚፈቅድ ህግ ከዚህ በፊት ያለው ሲሆን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በዚህ መንገድ ተወልደው ወደ ውጭ ሀገራት የሚሄዱ ህጻናት ቁጥር እየጨመረ ይገኛል ተብሏል።
ይህ ድርጊት በሩሲያ የሀይማኖት አባቶች ዘንድ በየጊዜው ተቃውሞ የሚገጥመው ሲሆን ህጉ የተፈጥሮ ጋር የሚጣረስ በመሆኑ መንግስት ህጉን እንዲከልስ ሲያሳስቡም ቆይተዋል።
በዚህም መሰረት የሀገሪቱ ህግ አውጪ ምክር ቤት በማህጸን ኪራይ አማካኝነት በሩሲያ ግዛት የተወለዱ ህጻናት ወደ ውጭ ሀገራት እንዳይጓዙ የሚከለክል ህግ ማርቀቁ ተገልጿል።
እስካሁን በሩሲያ ማህጸናቸውን አከራይተው ከተወለዱ ህጻናት መካከልም ከ45 ሺህ በላይ የሚሆኑት ወደ ተለያዩ የዓለማችን ሀገራት መወሰዳቸውን በዘገባው ላይ ተጠቅሷል።
አዲስ የተዘጋጀው ረቂቅ ህግ ሩሲያዊያን ማህጸናቸውን እንዳያከራዩ እና የተወለዱት ህጻናትም ወደ ውጪ ሀገራት እንዳይሰደዱ ይከለክላል ተብሏል።
የሩሲያ ታችኛው ምክር ቤት ቃል አቀባይ ቪያችስላቭ ቮሎዲን በብሄራዊ የእናቶች በዓል ላይ ባሰሙት ንግግር “ህጻናትን በምትክ እናት ሰበብ ወደ ውጪ ሀገራት መላክ ይቀራል ብለዋል።
እንደ ቃል አቀባዩ ገለጻ ካሳለፍነው ግንቦት ወር ጀምሮ ለውይይት የቀረበው አዲሱ ህግ በሀገሪቱ ላዕላይ ምክር ቤት ከጸደቀ በኋላ በፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ፊርማ እንደሚጸድቅ ይጠበቃል።
ይህ ህግ ከጸደቀ በኋላም ከሚቀጥለው ሳምንት ጀምሮ ስራ ላይ ሊውል እንደሚችልም ቃል አቀባዩ መናገራቸውን አርቲ ዘግቧል።