የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች የህክምና ቁሳቁሶችን ወደ ኢትዮጵያ ላከች
የድጋፍ ቁሳቁሶቹ ወገናቸውን ለማትረፍ ለሚታትሩ 33 ሺ ገደማ የጤና ባለሙያዎች የሚሆን ነው
የድጋፍ ቁሳቁሶቹ ዛሬ ምሽት አዲስ አበባ እንደሚደርሱ ይጠበቃል
የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች የህክምና ቁሳቁሶችን ወደ ኢትዮጵያ ላከች
የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች (ዩ.ኤ.ኢ) የኮሮና ቫይረስን በመከላከል ሂደት የኢትዮጵያን ጥረት ለማገዝ የሚያስችሉ የህክምና ቁሳቁሶችን ወደ አዲስ አበባ ልካለች፡፡
ወገናቸውን ለማትረፍ ለሚታትሩ 33 ሺ ገደማ የጤና ባለሙያዎች የሚሆን 33 ሜትሪክ ቶን ገደማ የድጋፍ ቁሳቁሶችን የጫነው አውሮፕላንም ዛሬ ምሽት ቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ እንደሚደርስ ይጠበቃል፡፡
አውሮፕላኑ ከዩ.ኤ.ኢ ለኢትዮጵያ የተላኩ 15 ሜትሪክ ቶን የድጋፍ ቁሳቁሶችን፣ለአፍሪካ ህብረት የተሰጡ 3 ሜትሪክ ቶን የህክምና ቁሳቁሶችን እንዲሁም ኢትዮጵያንና ሌሎች የአፍሪካ ሃገራትን ለመደገፍ ከዓለም የጤና ድርጅት የተላኩ 15 ሜትሪክ ቶን የድጋፍ ቁሳቁሶችን ጭኗል፡፡
ድጋፉ ዩ.ኤ.ኢ ከሌሎች ሃገራት ጋር በመተባበር የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት የሚደረጉ ዓለም አቀፍ ጥረቶችን ለማገዝ የጀመረችው ጥረት አካል ነው፡፡
ዩ.ኤ.ኢ አስቸኳይ ድጋፍ በሚያስፈልግባቸው አካባቢዎች ለሚደረጉ ሰብዓዊ ድጋፎች ቀዳሚ ትኩረት ሰጥታ ለመስራ ቁርጠኛ እንደሆነችም የኢትዮጵያ አምባሳደሯ መሃመድ ሳሊም ተናግረዋል፡፡
አምባሳደሩ “ከዓለም የጤና ድርጅት ጋር ባለን ትብብር በኩል የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት ጥረት እያደረገች ወዳለችው ኢትዮጵያ የድጋፍ ቁሳቁሶችን በማጓጓዛችን ኩራት ይሰማናል” ብለዋል፡፡
ድጋፉ ቫይረሱን በመዋጋቱ ሂደት የኢትዮጵያውያን የጤና ባለሙያዎችን ደህንነት ተጠብቆ ሙያዊ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ለማድረግ እንደሚያስችልም አምባሳደሩ ገልጸዋል፡፡
የዩ.ኤ.ኢ አመራርና ህዝብ ከኢትዮጵያና በቫይረሱ ከተጠቁ፤ ከደረሰባቸው ሰብዓዊ ድቀት ለማገገም ጥረትን በማድረግ ላይ ካሉ ሁሉም ሃገራት ጎን እንደሚቆምም ነው አምባሳደሩ በአጽንኦት የተናገሩት፡፡
እንደ ኤመራቲ የዜና ወኪል ዘገባ የዓለም የጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖምና የድርጅቱ የአደጋ ግዜ ስራዎች ዋና ዳይሬክተር ሪክ ብሬናን የዩ.ኤኢን ሰብዓዊ ተግባር አወድሰዋል፤ አመስግነዋልም፡፡