በእስካሁኑ ቆጠራ 65 በመቶውን ድምጽ በማግኘት ፕሬዚዳነት ሙሴቬኒ አርቲስት ቦብ ዋይንን እየመሩ ነው
በኡዳንዳ ትናንት የተካሄደው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ቆጠራ መጀመሩን የሀገረቱ የምርጫ ኮሚሽን አስታውቋል፡፡ እስካሁን ባለው ቆጠራ የሀገሪቱ ፕሬዚዳንት ዮዌሪ ሙሴቬኒ እየመሩ ነው፡፡
ቆጠራቸው ከተከናወነ ከ አንድ ነጥብ አምስት ሚሊዮን በላይ የድምጽ ካርዶች ውስጥ 65 በመቶውን በማግኘት ፕሬዚዳነት ሙሴቬኒ እየመሩ መሆናቸውን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
ተፎካካሪያቸው ሙዚቀኛው ሮበርት ክያጉላኒ ወይም በመድረክ ስሙ ቦቢ ዋይን 27 ነጥብ 39 የድምጽ ካርዶችን ማግኘት ችሏል፡፡ በሀገሪቱ አሁንም ድምጽ እየተቆጠረ ሲሆን በአጠቃላይ 34 ሺ 684 የምርጫ ጣቢዎች አሉ፡፡
የሀገሪቱ መንግስት ምርጫው ሰላማዊ መሆኑን ገልጿል፡፡ የዮዌሪ ሙሴቬኒ ተፎካካሪ ሮበርት ክያጉላኒ ግን ምርጫው መጭበርበሩንና ችግር እንደነበረበት ገልጿል፡፡ ይሁንና ሮበርት ክያጉላኒ ባቀረበው ቅሬታ ላይ ዝርዝር መረጃ አልሰጠም፡፡
እ.ኤ.አ ከ1986 ጀምሮላለፉት 35 ዓመታት ኡጋንዳን በፕሬዝዳንትነት የመሩት የ 76 ዓመቱ ሙሴቬኒ ምርጫውን በሰፊ ልዩነት እንደሚያሸንፉ ይጠበቃል፡፡