የኡጋንዳው ፕሬዝዳንት ዮዌሪ ሙሴቬኒ ተቃዋሚዎቻቸውን “አሸባሪዎች” ናቸው ሲሉ ወነጀሉ
በቁጥጥር ስር የዋሉት ምርጫን ተከትሎ ተቃዋሚዎች “ደብዛቸው”ጠፍተው የነበሩ ናቸው
ፕሬዘዳንቱ “አሸባሪዎች” ናቸው ያሏቸው 51 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ውለዋል
ፕሬዝዳንቱ ይህንን ያሉት በድህረገፃቸው ባሰፈሩት ጽሁፍ ሲሆን፡ 51 የሚሆኑ “ወንጀለኞች” ናቸው ተብለው የተጠረጠሩ ሰዎች በጸጥታ ኃይሎች አማካኝነት በቁጥጥር መዋላቸውም አረጋግጠዋል፡፡
ፕሬዝዳንቱ በቁጥጥር ስር ውለዋል ያሏቸው ሰዎች ታድያ በሀገሪቱ በወርሀ ጥር የተካሄደውን ምርጫ ተከትሎ ተቃዋሚዎች “ደብዛቸው ጠፍተዋል” ሲልዋቸው የነበሩ አባሎቻቸው እንደሆኑ ለማወቅ ተችለዋል፡፡
ፕሬዝዳንት ዮዌሪ ሙሴቬኒ አክለው ‘‘…ከእይታ ጠፍተው የነበሩት ሰዎች የክህደት ተግባር የፈጸሙ ተቀዋሚዎች ናቸው፤ እናም የችግሩ ምንጭና መነሻ ሳይመረምርና በተቃዋሚው አካል የተፈፀመ ክህድትና የሽብር ተግባር በውል ሳያጤን በፀጥታ ኃይሎቹ ስህተት ተፈፅሟል የሚል አካል ካለ እሱ ታማኝ ሰው አይደልም ’’ም ብለዋል፡፡
ተቃዋሚዎቹ እና የውጭ ደጋፊዎቻቸው የኡጋንዳ ዜጎች ፍላጎትን ሊቀለብሱ እንደነበር በጽሁፋቸው ያመለከቱት ፕሬዝዳንቱ፤የጸጥታ ኃይሎቹ የወንጀለኞቹ መዋቅር እንዲሁም የውጭ አዋኪዎች ከማፈራረስ አንፃር ከፍተኛ ሚና እየተጫወቱ መሆናቸውም አሳውቀዋል፡፡አሁን ላይ በቁጥጥር ስር የዋሉት ሰዎች ወንጀለኞችን ህግ ፊት ለማቅረብ ከባለስልጣኑ ጋር በትብብር እየሰሩ መሆናቸውንም ፕሬዘዳንቱ ገልጸዋል፡፡
ፕሬዝዳንት ዮዌሪ ሙሴቬኒ እንዲህ ይበሉ እንጂ በወንጀል የተጠረጠሩትን አካላት ለመያዝ የተደረገው ዘመቻ በበርካቶች ዘንድ የተተቸ ያልተገባ አካሄድ እንደነበር ይታወሳል፡፡ ዴይሊ ሞኒተር የተባለ የሀገሪቱ ሚድያ ድርጊቱን በማውገዝ ከተቹት ሚድያዎች የሚጠቀስ ነው፡፡