125ኛው የአድዋ ድል በዓል በኡጋንዳ ካምፓላ ተከበረ
አሁን ያለውን የቅኝ አገዛዝ ስልት ለማስቆም አፍሪካ ከድጎማ መላቀቅ እንዳለባት በምሁራን ተነስቷል
በኢትዮጵያ የሚታየው የጽንፈኛ ብሔርተኝነት አዝማሚያ ከአድዋ ድል መሠረት ጋር የሚጻረር እንደሆነ የኡጋንዳ ምሁራን ገልጸዋል
የጥቁር ህዝቦች የይቻላል እና የነጻነት ተምሳሌት እንደሆነ የሚነገርለት የአድዋ ድል 125ኛ ዓመት በኡጋንዳ ካምፓላ በፓናል ውይይት ተከብሯል፡፡
በኡጋንዳ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ከ ማከሬሬ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ባዘጋጀው በዚህ የፓናል ውይይት ላይ የኢትዮጵያ ም/ጠ/ሚ እና ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ፣ የባህል እና ቱሪዝም ሚኒስትር ሂሩት ካሳው (ዶ/ር) ፣ ኡጋንዳውያን የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ፣ ከኡጋንዳ የተለያዩ የሲቪል እና ሌሎች ተቋማት የተውጣጡ ተወካዮች እንዲሁም በኡጋንዳ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ታድመዋል፡፡
“የአድዋ ድል ለአፍሪካውያን” በሚል መሪ ቃል በተካሔደው ውይይት ፣ የአድዋ ድል እና ፓን አፍሪካኒዝም እንዲሁም የአድዋ ድል ለአፍሪካውያን ያለው ትርጉም በሚሉ ነጥቦችላይ በፓናሊስቶች የተለያዩ ሀሳቦች ተነስተዋል፡፡
በአሁኑ ጊዜ ያለውን የምዕራባውያንን ተጽዕኖ ለመቋቋም አፍሪካውያን ከአድዋ ድል ምን እንደሚማሩ የውይይቱ ተሳታፊዎች ለፓናሊስቶች ጥያቄዎችን በማንሳት ውይይት አድርገዋል፡፡
“አሁን ላይ በኢምፔሪያሊዝም ባርነት ተገዝተናል” ያሉት በማከሬሬ ዩኒቨርሲቲ የማህበራዊ ሳይንስ ምሁሩ አሲምዌ ጎድፍሬይ (ዶ/ር) ፣ ይህም በቀጥታ የሚተገበር ሳይሆን “ርዕዮተ ዓለማዊ ኢምፔሪያሊዝም ነው” ብለዋል፡፡
“ኢምፔሪያሊዝም በገንዘብ ድጎማ ተፈጻሚ እየሆነ ነው” ያሉት ሌላኛው ፓናሊስት ሳቢቲ ማካራ (ፕ/ር) ደግሞ አፍሪካ ከድጎማ መላቀቅ እንዳለባት እና የአህጉሪቱ ሀብት የህዝቦቿን ማንነት በማወቅ ለጉዞአቸው መዳረሻ በሚሆን መልኩ ጥቅም ላይ መዋል እንዳለበት ነው ሀሳባቸውን የሰጡት፡፡
“የአድዋ ድል ለአፍሪካ ብሄረተኝነት ጥናት እጅግ ጠቃሚ ነው” ያሉት የማከሬሬ ዩኒቨርሲቲ መምህሩ ምዋምቡጺያ ንዴቤሳ ድሉ በኡጋንዳ የትምህርት ካሪኩለም መካተቱንም ተናግረዋል፡፡ “አፍሪካ በአሁኑ ወቅት ከአውሮፓ ብቻ ሳይሆን ከእስያም ቢሆን የቅኝ አገዛዝ ሥጋት ውስጥ ናት” በማለት “የአድዋ ድል ቀጣይነት ያለው መነሳሳትን መፍጠር አለበት” ሲሉም ተናግረዋል፡፡
በአፍሪካ ጉዳይ የውጭ ኃይሎች ጣልቃ መግባታቸውን እንዲያቆሙ ማድረግ አህጉሪቱ በተለያዩ መስኮች ወደፊት መራመድ እንድትችል ሁነኛው መፍትሔ እንደሆነም ተነስቷል፡፡
በአድዋ ኢትዮጵያውያን በአንድነት ሆነው ፋሺስት ጣሊያንን ድል መንሳታቸው “ለአፍሪካዊ ችግሮች መፍትሔ” ማምጣት የሚቻለው በጋራ በመቆም መሆኑን እንደሚያመለክት ነው ፓናሊስቶቹ የተናገሩት፡፡
በኢትዮጵያ አሁን አሁን የሚንጸባረቁ የጽንፈኛ ብሔርተኝነት አካሔዶች ፣ በብሔር የመከፋፈል እና የመጋጨት አዝማሚያዎች ለሀገሪቱ ከፍተኛ አደጋ መሆናቸውንም በውይይቱ የተሳተፉ ምሁራን አንስተዋል፡፡ ይህ አዝማሚያ የአድዋ ድል ከሆነው የአንድነት መሠረት ጋር የሚጻረር እና የሀገሪቱን ገጽታም የሚያበላሽ እንደሆነ በመግለጽ ዘላቂ እልባት እንደሚያሻውም ምክረ-ሀሳባቸውን ለግሰዋል፡፡
በበይነ መረብ በውይይቱ ላይ የተሳተፉት ኢትዮጵያዊው ሹመት ሲሻኝ (ፕ/ር) ፣ ጦርነቱ የተካሔደው ለዓለም ግልጽ ባልሆነ ስፍራ ላይ ቢሆንም የአድዋ ድል ግን 24 ሰዓት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ መላውን ዓለም ማዳረሱን አንስተዋል፡፡ የአፍሪካውያን የነጻነት ምልክት የሆነው ይህ ድል የአውሮፓን ጥቅም ለማስጠበቅ አፍሪካውያንን እርስ በእርስ ማጋጨት የሚለው የቅኝ ገዢዎች አስተሳሰብ እንደማይሰራ የታየበት መሆኑንም ነው ፕሮፌሰሩ የተናገሩት፡፡
የአድዋ ድል ለነጻነት በሚደረጉ እንቅስቃሴዎች በራስ መተማመንን መፍጠሩን ያስታወሱት የኡጋንዳ የደህንነት ሚኒስትር ጄኔራል ኤሊ ቱምዋይን “አፍሪካ ደካማ ፣ ጥገኛ እና ራሷን መከላከል የማትችል” እንደሆነች የሚታሰበውን ትርክት የቀየረውን ይህን ድል ከማክበር ባለፈ “አስተሳሰቡ ለልጆቻችን እንዲተላለፍ ማድረግ አለብን” ብለዋል፡፡ “አድዋ ምን ተግባራትን ለምን ዓላማ እንደምናከናውን የምንማርበት መሆን አለበት” ሲሉም ነው የተናገሩት ጄኔራሉ፡፡
“የአድዋ ጦርነት የተባበረ ህዝብ ምን ያህል ማሳካት እንደሚችል ያሳያል” ያሉት በኡጋንዳ የኢትዮጵያ አምባሳደር አለምጸሐይ መሰረት “ድሉ ዛሬ ላይ አፍሪካውያንን ለማብቃት እና ፓን አፍሪካኒዝምን ለማንቃት ጠቃሚ ነው” ሲሉ ገልጸዋል፡፡
የአድዋ ድል የተገኘው በጠንካራ እና በጥሩ አመራር መሆኑን ያነሱት ፓናሊስቶቹ አፍሪካዊ አንድነት መጠናከር እንዳለበት እና ይህም በጠንካራ ተቋማዊ አደረጃጀት ሊመራ እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡
ውይይቱ በኡጋንዳው ኤንቢኤስ ቴሌቪዥን በቀጥታ ስርጭት ተላልፏል፡፡