ባለፉት 3 ሳምንታት ብቻ በዩኬ ከ 21 ሺ በላይ ሰዎች በኮሮና ህይወታቸውን አጥተዋል
ሆስፒታሎች በመጨናነቃቸው ሀገሪቱ ታማሚዎችን ወደ ሆቴሎች እንደምታዛውር ከሰሞኑ መግለጿ ይታወሳል
በሦስት ሳምንታት በቫይረሱ የተያዙ የሀገሪቱ ዜጎች ቁጥር ደግሞ ከ 1 ሚሊዮን በላይ መሆኑ ተገልጿል
በአሁኑ ወቅት የኮሮናቫይረስ ክፉኛ እየተፈታተናት የምትገኘው ዩኬ (ብሪታኒያ) ፣ የቫይረሱ ተጠቂዎች እና ሟቾች ቁጥር በከፍተኛ መጠን እያሻቀበባት ነው፡፡
ሀገሪቱ 2021 ከገባ ወዲህ ባሉት ሦስት ሳምንታት ብቻ 21,024 ዜጎቿን በቫይረሱ አጥታለች፡፡ ይህም ብሪታኒያን አዲሱ ዓመት ከገባ ወዲህ ከፍተኛውን ሞት ያስተናገደች ሀገር ያደርጋታል፡፡
ባለፈው ማክሰኞ ብቻ 1,610 ፣ ረቡዕ ዕለት ደግሞ 1,820 ሞት በማስመዝገብ በተከታታይ ካለፉት ጊዜያት ጋር ሲነጻጸር ከፍተኛውን ዕለታዊ የሟቾች ቁጥር አስተናግዳለች፡፡
በዚህ ሳምንት ብቻ 283,388 አዲስ የኮሮና ተጠቂዎች የተገኙባት ዩኬ ፣ ባለፉት ሦስት ሳምንታት ያስመዘገበችው የቫይረሱ ተጠቂዎች ቁጥር 1,054,866 ደርሷል፡፡
ዎርልድ ሶሻሊስት ዌብ ሳይት እንደዘገበው አሁን ላይ በቬንትሌተር ታግዘው ህይወትን እየገፉ የሚገኙ ሰዎች ቁጥር 3,947 ነው፡፡
ሆስፒታሎች የኮሮና ታማሚዎችን ማስተናገድ ካለመቻላቸው ጋር ተያይዞ ፣ የቅርብ ክትትል ከሚያስፈልጋቸው ውጭ ታማሚዎችን ወደ ሆቴሎች እንደምታዛውር ሀገሪቱ ከሰሞኑ መግለጿ ይታወሳል፡፡ የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት በሚል በሀገሪቱ በርካታ እገዳዎች መጣላቸው የሚታወቅ ሲሆን እገዳው ሊቆይ እንደሚችል ጠቅላይ ሚኒስትር ቦርስ ጆንሰን ገልጸዋል፡፡
እስካሁን በ ዩኬ ከ 3.5 ሚሊዮን በላይ ሰዎች በቫይረሱ ሲያዙ ከ94 ሺ በላይ ሰዎች ደግሞ ህይወታቸውን አጥተዋል፡፡