ወደ ኮቪድ የሚያደርሰውን የቫይረስ ‘ኢንፌክሽን’ ይከላከላል የተባለ መድሃኒት በብሪታንያ እየተሞከረ ነው
በአሁኑ ሰዓት በሙከረ ላይ የሚገኘው ይህ መድሃኒት እስከ መጋቢት አገልግሎት ላይ ሊውል እንደሚችል ይጠበቃል
መድሃኒቱ ለኮሮና በተጋለጠ ግለሰብ ላይ ቫይረሱ ሳይጎለብት በፍጥነት ለመከላከል የሚረዳ ነው ተብሏል
ለኮሮናቫይረስ የተጋለጠ ሰው የሚያሳያቸው ምልክቶች (ኢንፌክሽኖች)ወደ ኮሮናቫይረስ ደረጃ ሳይደርሱ ኢንፌክስኑን ይከላከላል የተባለ መድሃኒት በመሞከር ላይ መሆናቸውን የብሪታንያ ሳይንቲስቶች ገለጹ፡፡ ይህም በርካታ ህይወት ይታደጋል የሚል እምነት ተጥሎበታል፡፡
የፀረ እንግዳ አካላት ሕክምናው (መድሃኒቱ) ፣ በሽታው ሳይጎለብት በፍጥነት ለመከላከል የሚረዳ ሲሆን በሆስፒታል ለሚገኙ ህመምተኞችእና በቤት ውስጥ ለሚታከሙ በድንገተኛ ህክምና መልክ ይሰጣል ነው የተባለው፡፡
በኮቪድ የተያዘ ሰው በሚኖርበት ቤት ውስጥ በአንድ ላይ የሚኖሩ የቤተሰብ አባላትም ፣ በበሽታው እንዳይያዙ መድኃኒቱን ሊከተቡ ይችላሉ ብለዋል ሳይንቲስቶቹ፡፡ እንዲሁም አብረው ስለሚኖሩ ፣ ስለሚያጠኑ እና በአንድነት ሌሎች የተለያዩ ተግባራትንም ስለሚያከናውኑ ቫይረሱ በፍጥነት የመስፋፋት እድል ስላለው፣ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችም ክትባቱ ሊሰጣቸው ይችላል፡፡
መድሃኒቱን ከአስትራ ዜንካ ጋር በመሆን የሚያዘጋጀው የለንደን ሆስፒታሎች ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ተመራማሪ ዶ / ር ካትሪን ሁሊሃን "ይህ ህክምና የሚሰራ መሆኑን ማረጋገጥ እና ለኮቪድ -19 በሽታ ለሚዳርገው ቫይረስ የተጋለጡ ሰዎችን መከላከል ከቻልን ፣ ይህን አስፈሪ ቫይረስ ለመዋጋት እየተዘጋጁ ላሉ የምርምር ውጤቶች አስደሳች ተጨማሪ ጤት ነው" ብለዋል፡፡
መድሃኒቱ ውጤታማነቱ ተረጋግጦ እውቅና ከተቸረው ለኮሮና ቫይረስ ከተጋለጡ እስከ 8 ቀናትን ላስቆጠሩ ግለሰቦች እንደሚሰጥ ተገልጿል፡፡ ፈቃድ ካገኘ በቀጣዩ መጋቢት ወይም ሚያዝያ ወር አገልግሎት ላይ ይውላል ተብሏል፡፡ በአሁኑ ሰዓት መድሃኒቱ ለቫይረሱ በተጋለጡ ሰዎች ላይ ሙከራ እየተደረገለት እንደሆነ ዘ ጋርዲያን ዘግቧል፡፡