የሩሲያ መከላከያ ሚኒስቴር ጥቃት ለማድረስ የተላኩትን የዩክሬን ድሮኖች መትቶ መጣሉን ገልጿል
የዩክሬን ሶስት ድሮኖች ዛሬ ማለዳ በሩሲያ መዲና ሞስኮ ጥቃት ለማድረስ መሞከራቸው ተገለጸ።
የሩሲያው ታስ እንዳስነበበው በድሮን ጥቃቱ በአንድ ሰው ላይ ጉዳት ደርሷል።
በሁለት ህንጻዎች ላይም ቀላል ጉዳት መድረሱን የሞስኮ ከተማ ከቲባ ሰርጌ ሶብያኒን ተናግረዋል።
የድሮን ጥቃት ሙከራውን ተከትሎ ቭኑኮቭ የተሰኘው አውሮፕላን ማረፊያ በጊዜያዊነት መዘጋቱ ነው የተገለጸው።
ኬቭ በሞስኮ ከተማ ላይ በአንድ ሳምንት ውስጥ ሶስተኛውን የድሮን ጥቃት ለማድረስ ሞክራለች።
ጥቃቱን “የሽብር ጥቃት ሙከራ ነው” ያለው የሩሲያ መከላከያ ሚኒስቴር አንዷ ድሮን ተመታ መውደቋን አስታውቋል።
ሁለቱ ድሮኖች ደግሞ በሞስኮ የገበያ ማዕከል ላይ መውደቃቸውን ነው የገለጸው።
ዩክሬን ባለፈው ሳምንት ሰኞ ወደ ሞስኮ ከላከቻቸው ሁለት ድሮኖች አንደኛው ከክሬምሊን በ3 ኪሎሜትር ርቀት ላይ መውደቁ ይታወሳል።
ሌላኛው ድሮንም በደቡባዊ የከተማዋ ክፍል የሚገኝ ረጅም ህንጻ ላይ ጉዳት ማድረሱን አሶሼትድ ፕረስ አስታውሷል።
ኬቭ ለዛሬውም ሆነ ከዚህ ቀደም በሞስኮ ላይ ለፈጸመቻቸው የድሮን ጥቃት ሙከራዎች ሃላፊነቱን አልወሰደችም።
18ኛ ወሩን በያዘው የሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት የአየር ሃይሏ የተዳከመው ዩክሬን ድሮኖችን እንደ ዋነኛ የማጥቂያ መሳሪያ እየተጠቀመች ነው።