ተመድ በጦርነቱ ምክንያት በትግራይ፣ አማራ እና አፋር “በሚፈለገው ደረጃ እርዳታ ማዳረስ አልቻልኩም” አለ
የኮሚሽኑ ቃል አቀባይ በርካቶችን እያፈናቀለ ያለው ጦርነት ቆሞ የእርዳታ ሰራተኞች መንቀሳቀስ መቻል አለባቸው ብለዋል
ኮሚሽኑ የተመድ የሰብአዊ አየር አገልግሎት በረራ በመቆሙ በተለይም በትግራይ ያለው ሁኔታ አሳሳቢ አደርጎታል ብሏል
ባለፈው ነሀሴ ወር አጋማሽ ላይ በሰሜን ኢትዮጵያ ዳግም የተቀሰቀሰውን ጦርነት ተከትሎ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ቀያቸውን ለቀው ተፈናቅዋል፡፡
ኢትዮጵያ የተመድ የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን ቃል አቀባይ ኔቨን ክሬቨንኮቪች ዳግም ባገረሸው ጦርነት ምክንያት በትግራይ፣ አማራ እና አፋር በሚፈለገው ደረጃ እርዳታ ማዳረስ እንዳልተቻለ ለአል-ዐይን አማርኛ ተናግረዋል፡፡
በተለይም ወደ ትግራይ ሲደረግ የነበረው የተመድ የሰብአዊ አየር አገልግሎት በረራ በመቆሙ ምክንያት በግጭቱ ለተጎዱ ዜጎች የህይወት አድን እርዳታ የሚሰጡ የዩኤንኤችሲአርን ጨምሮ ሌሎች ግብረሰናይ ሰራተኞች ወደ ትግራይ ክልል መግባት ባለመቻላቸውና የጥሬ ገንዘብ እቅረቦት ባለመኖሩ ችግሩን ይበልጥ አሳሳቢ አድርጎታል ብለዋል ቃል አቀባዩ፡፡
ያም ሆኖ ጦርነቱ ካገረሸበት ጊዜ አንስቶ ኮሚሽኑ በሶስቱም ክልሎች ባሉት አስር ቦታዎች ሆኖ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ለመስራት እየሞከረ መሆኑ ገልጸዋል ቃል አቀባዩ፡፡
ቃል አቀባዩ እንደገለጹት ኮሚሽኑ“በቅርቡ በትግራይ የሚገኘው ቡድን ከተፈናቃዮች እና ከአከባቢው ማህበረሰቦች ለተውጣጡ ሴቶች እና ልጃገረዶች የሚገኙባቸው 7 ሺህ ተፈናቃዮች (በመቀሌና ሽሬ) የንጽህና እና አስቸኳይ የመጠሊያ ቁሳቁሶች አከፋፍሏል፡፡
ዩኤንኤችሲአር ከአጋሮቹ ጋር በመሆን ወደ አፋር ክልል (ጉሊና ወረዳ) ከክልሉ ባለስልጣናት ጋር በመቀናጀት 2ሺህ 500 ለሚሆኑ አዲስ ተፈናቃዮችን የጸሐይ ብርሃን መብራቶችን(ሶላር)፣ ብርድ ልብሶችን፣ ባልዲዎችን፣ የመኝታ ምንጣፎችን፣ የወባ ትንኝ መረቦችን፣ እና የንጽህና ቁሳቁሶች ልኳል”ም ብለዋል፡፡፡
በተጨማሪም በሰመራ የነበሩት 6ሺህ የሚሆኑ ተፈናቃዮች ከነሐሴ 16 እስከ መስከረም 5 ባለው ጊዜ ውስጥ ወደ አብዓላ እንዲሁም በሎግያ ከተማ የሚኖሩ 60 ተፈናቃዮች በመንግስት መሪነት ወደ በራህሌ እንዲመለሱ በማድረግ በኩል የትራንስፖርት ድጋፍ፣ የውሃ እና የምግብ ድጋፍ ማድረጉ አስታውቀዋል፡፡
ኔቨን ክሬቨንኮቪች፤ በአማራ ክልልም በክልሉ የሚገኘው ዩኤንኤችዲአር እ እና አጋር ድርጅቶች በደቡብ ወሎ ወረዳ በሚገኙ ዘጠኝ ቦታዎች ለአዲስ ገቢዎች መሰረታዊ የእርዳታ ቁሳቁሶችን በማከፋፈል ላይ መሆናቸው ተናግረዋል።
አሁን የተቀሰቀሰው ጦርነት ብዙ ሰዎች ለደህንነት እና ለሰብአዊ እርዳታ ፍለጋ ቤታቸውን ጥለው እንዲሰደዱ ያስገደደ ነው ያሉት ቃል አቀባዩ፤ የሰብአዊ ርዳታ ሰራተኞች በሚሊዮን የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያንን በህይወት አድን ርዳታ ደርሰዋል፡፡
ቃል አቀባዩ ለዚህ ቀውስ ሁሉ ምክንያት የሆነው ጦርነት በአስቸኳይ እንዲቆም ጠይቀዋል፡፡