ወደ ትግራይ የሚደረገው የሰብአዊ እርዳታ ጉዞ መቆሙን የተመድ የሰብአዊ ጉዳዮች ቢሮ አስታወቀ
መንግስት እና ህወሓት ተኩስ አቁሙን በመጣስ እየተካሰሱ ነው
በአማራ እና በአፋር ክልሎች ሰዎች እየተፈናቀሉ መሆናቸውን ያልተረጋገጡ ሪፖርቶች እንደደረሰው ቢሮው ገልጿል
የተባበሩት መንግስት ድርጅት(ተመድ)የሰብአዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ቢሮ እንዳስታወቀው በየብስ እና በአየር ወደ ትግራይ ሲደረግ የቆየው የሰብአዊ እርዳታ ጉዞ መቆሙን አስታውቋል።
በየብስ የሰብአዊ እርዳታ ከባለፈው ሀሙስ ጀምሮ የቆመ ሲሆን በአየር የሚደረገው እርዳታ ደግሞ አርብ ጀምሮ መቆሙን ቢሮ ገልጿል።
ቢሮው እንቅስቃሴ በመቆሙ ምክንያት የእርዳታ ሰራተኞችን እንቅስቃሴ አስተጓጊሏል ብሏል።
አስቸኳይ ተኩስ አቁም እንዲደረግ የጠየቀው ቢሮው የጸጥታው ሁኔታ የሚፈቅድ ከሆነ ቢሮው ከአጋሮቹ ጋር በመሆን ለተጎዱ ሰዎች እርዳታ እንደሚያቀርብ ገልጿል።
በአማራ በአፋር ክልሎች በጦርነት ቀጣና ያሉ ሰዎች እተፈናቀሉ መሆናቸውን ያልተረጋገጡ ሪፖርቶች እንደደረሱት የገለጸው ቢሮው በሰሜን ኢትዮጵያ ያለው የሰብአዊ ሁኔታ አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሷል ብሏል።
በፌደራል መንግስት እና በሽብርተኝነት በተፈረጀው ህወሓት መካከል የነበረው ግጭት ለወራት ጋብ ብሎ የነበረ ቢሆንም ባለፈው ሳምንት በድጋሚ ተቀስቅሷል።
የህወሓት ኃይሎች የቆቦ ከተማን መያዛቸውን እና ወደ ፊት ጦርነት እያከሄዱ መሆናቸውን ነዋሪዎች ተናግረዋል። የህወሓት ታጣቂዎች በቆቦ ከተማ ንጹሃንን መግደላቸውን ነዋሪዎች ለአል ዐይን አማርኛ በትናንትናው እለት ተናግረዋል።
ህወሓት ተፈጽሟል በተባለው ግድያ ዙሪያ ያለው ነገር የለም።
የፌደራል መንግስት ህወሓት የሰላም አማራጭን ወደ ጎን በመተው ጥቃት መሰንዘሩን ገልጾ ከቆቦ ከተማ የከተማ ውጊያ ላለማድረግ ማፈግፈጉን መግለጹ ይታወሳል።
መንግስት የህወሓትን ጥቃት እየመከተ እንደሚገኝም እየገለጸ ነው።
በአማራ ክልል በሰቆጣ፣በወልዲያ፣ በደሴ እና በከምቦልቻ ከጦርነቱ ጋር በተያያዘ ሰጋት የሰአት እለፊ ገደብ ተጥሏል።
ሁለቱም አካለት ለወራት የዘለቀውን የተናጠል ተኩስ አቁም በመጣስ አንደኛው ሌላኛውን በመወንጀል ላይ ናቸው።
ቢሮው ወደ ትግራይ የሚያደርገውን ሰብአዊ እርዳታ ማቆሙን የገለጸው ጦርነቱ እንደገና በመቀስቀሱ ምክንያት ነው።
ግጭቱን በድርድር ለመቋጨት ሁለቱም አካላት በተናጠል ሲገልጹ የቆዩ ቢሆንም ዳግም ወደ ግጭት ገብተዋል።
የአፍሪካ ህብረት ግጭቱን በድርድር ለመፍታት ሁቱንም አካላት በተደጋጋሚ ያገኘ ቢሆንም እስካሁን ተጨባጭ ውጤት አላመጣም።
ህወሓት ለመደራደር ያለውን ዝግጁነት የገለጸ ሲሆን በህብረቱ ላይ ግን የገለልተኝነት ጥያቄ አንስቷል።