ህወሓት፤ በትግራይ መሠረተ ልማቶችን መልሶ ለመገንባት ለሚሰማሩ አካላት የደህንነት ዋስትና እሰጣለሁ አለ
ደብዳቤው መቀሌን ለመጀመሪያ ጊዜ በጋራ ለጎበኙ የአሜሪካ እና የአውሮፓ ልዩ መልዕክተኞች አማካኝነት የተላከ ነው
ደብዳቤውን ከሊቀመንበሩ መቀበላቸውን ያስታወቁት ልዩ መልዕክተኞቹ ጉዟቸውን የተመለከተ የጋራ መግለጫ አውጥተዋል
የህወሓት ሊቀመንበር ደብረጽዮን ገብረ ሚካኤል (ዶ/ር) በትግራይ የመብራት እና ሌሎችንም መሠረተ ልማቶች መልሶ ለመገንባት ለሚሰማሩ አካላት የደህንነት ዋስትና እንደሚሰጡ በደብዳቤ ገለጹ፡፡
ሊቀመንበሩ ዋስትናው መስጠታቸውን የሚገልጸውን ደብዳቤ ክልሉን በጎበኙ፤ በአፍሪካ ቀንድ የአሜሪካ እና የአውሮፓ ህብረት ልዩ መልዕክተኞች በኩል ለፌዴራሉ መንግስት መላካቸውን የአሜሪካ እና የአውሮፓ ህብረት ባወጡት የጋራ መግለጫ አስታውቀዋል፡፡
ልዩ መልዕክተኞቹ የፌዴራል መንግስቱ እና ህወሓት በአፍሪካ ህብረት ጥላ ስር ለመነጋገር የያዙትን ውጥን ለማበረታታት በማሰብ ወደ መቀሌ መጓዛቸውን ባስታወቁበት መግለጫቸው በሁለቱም አካላት በኩል ለመነጋገር የታየውን ቁርጠኝነት አድንቀዋል።
ግጭቱን በማቆም ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን የፓለቲካዊ ምክክሮችን ማድረጉ እንደሚበጅም ነው የገለፁት።
ማይክ ሐመርን እና አኒታ ዌበርን እንዲሁም በኢትዮጵያ የመንግስታቱ ድርጅት ተወካዮችን፣ የካናዳ እና የጣሊያን አምባሳደሮችን ያካተተው ልዑኩ በመቀሌ ከዶ/ር ደብረጽዮን እና ከሌሎችም ከፍተኛ የህወሓት አመራሮች ጋር ተወያይቷል።
በውይይቱ ዶ/ር ደብረጽዮን ግጭቱን እና ድርድሩን በተመለከተ ያላቸውን አቋም ለልዑካኑ አስረድተዋል።
ልዩ መልዕክተኞቹም በጋራ መግለጫቸው የመብራት፣ የባንክ እና ሌሎችም አገልግሎቶች በቶሎ መጀመር እንዳለባቸው መስማማታቸውን ገልፀዋል፤ ቀደም ሲል ከፌዴራል መንግስቱ ባለስልጣናት ጋር በነበራቸው ውይይት ጉዳዩ እውቅና መሠጠቱን በማስታወስ።
በዚህን ጊዜም ነው ዶ/ር ደብረጽዮን አገልግሎቱ ሊመለስ የሚችልባቸውን መሠረተ ልማቶች መልሶ ለመገንባት ለሚሰማሩ አካላት የደህንነት ከለላ ለማድረግ ዋስትና እንሰጣለን የሚል የማረጋገጫ ደብዳቤን ለልዩ መልዕክተኞቹ የሰጡት። ደብዳቤው ለፌዴራሉ መንግስት የተላከ ነው።
ዶ/ር ደብረጽዮን ከልዑካኑ ጋር ፍሬያማ ውይይት ማድረጋቸውን የህወሓት ቃል አቀባይ አቶ ጌታቸው ረዳ በይፋዊ የትዊተር ገጻቸው አስፍረዋል።
የጋራ መግለጫው በትግራይ፣ በአፋር እና በአማራ ክልሎች ሰብዓዊ እርዳታዎች ሳይቆራረጡ ሊቀርቡ እና በገንዘብ፣ ነዳጅ እና የአፈር ማዳበሪያ ላይ የተጣሉ ገደቦች ሊነሱ እንደሚገባ ያትታል።
አሜሪካ እና ህብረቱ በድርቅ በተጎዱና ለምግብ ዋስትና ችግር በተዳረጉ አካባቢዎች ጭምር ድጋፍ ለማድረግ ቁርጠኛ ስለመሆናቸውም በመግለጫው ተጠቅሷል።
ልዩ መልዕክተኞቹ ተጠያቂነት ለእርቅ መሠረት መሆኑን በማስታወስ የተፈጸሙ ጥፋቶችን ለመመርመር ለሚሰማሩ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች መርማሪ ባለሙያዎችን መተባበር እንደሚገባ አሳስበዋል።
ሁሉም አካላት ከጥላቻ እና ፀብ አጫሪ ድርጊቶች እንዲቆጠቡም አስጠንቅቀዋል።
ልዩ መልእክተኞች ደብዳቤ መቀበላቸውን ቢገልጹም ለመንግስት ማድረስ ወይም አለማድረሳቸውን አልገለጹም፡፡የፌደራል መንግስት ደብዳቤውን በተመለከተ ያለው ነገር የለም፡፡
የፌደራል መንግስት እና ህውሓት በተናጠል በኢትዮጵያ የተፈጠረውን ግጭት በድርድር ለመቋጨት ያላቸውን ፍላጎት ገልጸዋል፡፡
መንግስትን የሚመራው ብልጽግና ፓርቲ ከህወሓት ጋር ለመደራደር በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን የሚመራ ቡድን መቋቋሙን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በህዝብ ተወካዮች ም/ቤት በቀረቡበት ወቅት መናገራቸው ይታወሳል
ህወሓት፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ መንግስታቸው ለመደራደር መፈለጉን ከመግለጻቸው ቀደም ሲል በኬንያ አስተናጋጅነት እና አመቻችነት ለሚደረገው ድርድር ዝግጁ መሆኑን ገልፆ ነበር፡፡
መንግስት ድርድሩ በአፍሪካ ህብረት ብቻ ይመራ ሲል ህወሓት ግን በዚህ እንደማይስማማ ገልጿል፡፡