ሶስቱም ሀገራት ካልጋበዟት በግድቡ ድርድር መግባት እንደማትችል አሜሪካ አስታወቀች
አሜሪካ፤ ዓባይ ለግብፅ ብቻ ሳይሆን ለኢትዮጵያ እና ሱዳንም ወሳኝ ወንዝ ነው ብላለች
ኢትዮጵያ፣ሱዳን እና ግብፅ ካልጋበዟት በሕዳሴ ግድብ ድርድር ላይ መሳተፍ እንደማትችል አሜሪካ አስታወቀች
የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት የቀጠናዊ ጉዳዮች ቃል አቀባይ ሳሙኤል ዋርበርግ፤ ሀገራቸው ዓባይ ለግብፅ ብቻ ሳይሆን ለኢትዮጵያ እና ሱዳንም ወሳኝ ወንዝ እንደሆነ እንደምታምን አስታውቀዋል፡፡ በመሆኑም ሶስቱም ሀገራት አሜሪካን ለውይይት ካልጠሯት ለመሳተፍ እንደማትችልም ነው ቃል አቀባዩ የገለጹት፡፡
አዲስ አበባ፤ ካርቱም እና ካይሮ ፤ ዋሸንግተን ታደራድረን የሚል ጥሪ ካላደረጉ በስተቀር በሕዳሴ ግድብ ጉዳይ ጣልቃ የምትገባበት ሁኔታ እንደማይኖር አስታውቀዋል፡፡
ይሁንና ሶስቱም ሀገራት ግብዣ የሚቀርቡ ከሆነ ለውጤታማነቱ አዎንታዊ ሚና ለመጫወት ዝግጁ መሆኗንም ቃል አቀባዩ ይፋ አድርገዋል፡፡ ቃል አቀባዩ ቴን ከተባለ ቴሌቭዥን ጣቢያ ጋር ባደረጉት ቃለ መጠይቅ የሕዳሴ ግድብ ድርድር መፍትሄ የሚገኘው በሶስቱ ሃገራት መካከል በሚደረግ ንግግር እንደሆነ አሜሪካ እምነት እንዳላት ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲም ከሰሞኑ በሰጡት መግለጫ ኢትዮጵያ ለሶስትዮሽ ድርድር ምንጊዜም ዝግጁ መሆኗን መግለጻቸው ይታወሳል፡፡ ከዚህ ባለፈም ሱዳን እና ግብጽ፤ የአውሮፓ ሕብረት፤ አሜሪካ እና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በአደራዳሪነት እንዲገቡ ያቀረቡት ሀሳብ በይፋ እንዳልቀረበ ገልጸው ነበር፡፡ ኢትዮጵያ የሕዳሴ ግድብ ድርድር በአፍሪካ ሕብረት ብቻ መሆን እንዳለበት ጽኑ አቋም እንዳላት መገለጹ ይታወሳል፡፡
የሕዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ዋና ሥራ አስኪያጅ ኢ/ር ክፍሌ ሆሮ የግድቡ ግንባታ 78 ነጥብ 8 በመቶ መድረሱን ትናንት የገለጹ ሲሆን ሁለተኛው ዙር የውኃ ሙሌትም በተያዘለት ገዜ እንደሚከናወን ተገልጿል፡፡