ሱዳን አራት አካላት በግድቡ ዙሪያ በአደራዳሪነት እንዲሳተፉ ያቀረበችውን ሀሳብ ግብጽ መደገፏን ገለጸች
ካርቱም የሚገኙት የግብፅ ፕሬዝዳንት አብዱልፈታህ አልሲሲ እና የሱዳን የሉዓላዊ የሽግግር ምክር ቤት ሊቀመንበር አብዱልፈታህ አል ቡርሀን በሕዳሴ ግድብ ጉዳይ የአንድ ወገን እርምጃ ተቀባይነት እንደሌለው ገለጹ፡፡
አልሲሲ እና አልቡርሃን በካርቱም ቤተመንግስት ውይይት ካደረጉ በኋላ ባልተለመደ ሁኔታ በኢትዮጵያ ግድብ ዙሪያ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡ የሕዳሴ ግድብ ድርድር ሂደት አሁን ችግር ላይ በመሆኑ የሁለቱንም ሀገራት ትብብር እንደሚጠይቅ አስታውቀዋል፡፡
ከሰሞኑ ሱዳን በሕዳሴ ድርድር ከአፍሪካ ሕብረት በተጨማሪም አሜሪካ፣ የአውሮፓ ሕብረት እና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት እንዲሳተፉ ያቀረበችውን ሀሳብ ግብፅ እንደምትደግፍም ዛሬ ፕሬዝዳንቷ መግለጻቸውን የወጣው መግለጫ ያመለክታል፡፡
መሪዎቹ የዓባይን ወንዝ በብቸኝነት ለመቆጣጠር የሚደረግን ጥረት እንደማይቀበሉም ነው በመግለጫው ላይ ያስታወቁት፡፡ የግብፅ ፕሬዝዳንት እና የሱዳን የሉዓላዊነት የሽግግር ምክር ቤት ሊቀመንበር ሁለትዮሽ ፣ ቀጠናዊና ዓለም አቀፋዊ ጥረት በማድረግ በሕዳሴ ግድብ ሙሌት እና አስተዳደር ላይ ስምምነት እንዲመጣ ለማድረግ ተስማምተዋል፡፡
ምንም እንኳን የተነሱ ጉዳዮች በመግለጫው ላይ በግልጽ ባይጠቀሱም የግብፁ ፕሬዝዳንት እና የሱዳኑ ሉዓላዊ የሽግግር ምክር ቤት ሊቀመንበር በኢትዮጵያ እና በሱዳን ድንበር ላይ ባሉ ወቅታዊ ሁኔታዎች ዙሪያ ተወያተዋል ብሏል መግለጫው፡፡ ከዚህ ባለፈም ካርቱምና ካይሮ የሁለትዮሽ ግንኙነታቸውን ለማጠናከርም መነጋገራቸውን መግለጫው አካቷል፡፡
አብዱል ፈታህ አልሲሲ የቀድሞው የሱዳን መሪ ኦማር ሀሰን አልበሽር ከስልጠን ከተወገዱ በኋላ ወደ ካርቱም ሲመጡ ይህ የመጀመሪያቸው ነው፡፡ አልሲሲ ወደ ካርቱም ሲገቡ በከተማዋ ያሉ ዋና ዋና መንገዶች በሙሉ ዝግ እንደነበሩ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል፡፡