“ሱዳን ከሕዳሴ ግድብ ጋር በተያያዘ ወደ ሁለተኛ አማራጭ እየተሸጋገረች ነው” ሱዳናዊው የፖለቲካ ተንታኝ ኦስማን ማርጋኒ
“ከዚህ በኋላ ሱዳን አዲስ የዲፕሎማሲ ዘዴን የምትጠቀም አይመስለኝም” ሲሉም ገልጸዋል
ሱዳን የውሃ ብክነትን ለማካካስ የጥንቃቄ እርምጃዎችን የመውሰድ እቅድ ወደ መተግበር እየገባች እንደሆነ ተንታኙ ተናግረዋል
ሱዳን ከኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ጋር በተያያዘ ወደ ሁለተኛ አማራጭ እየተሸጋገረች መሆኑን ሱዳናዊው የፖለቲካ ተንታኝ ኦስማን ማርጋኒ ተናገሩ።
ኦስማን ማርጋኒ የፖለቲካ ተንታኝ እና የአል-ታይያር ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ናቸው፡፡ በኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ እና በወቅታዊ ሁኔታዎች ዙሪያ ከስካይ ኒውስ አረቢክ ጋር ቆይታ አድርገዋል። በዛሬው እለት የሕዳሴ ግድብ 10ኛ ዓመትን በማስመልከት በአዲስ አበባ በተካሔደው ሲምፖዚየም ላይ ከተነሱ ሀሳቦች ጋር በማያያዝ ነው ተንታኙ ስካይ ኒውስ ቀርበው አስተያየታቸውን የሰጡት፡፡
በቆይታቸውም ዛሬ የኢትዮጵያ ባለስልጣናት ከሰጡት መግለጫ በመነሳት “ካርቱም አሁን ላይ በግድቡ ግንባታ እና የድርድር ሂደቱ ላይ የአዲስ አበባን የቆየ እና የማይለዋወጥ አቋም እንደምትረዳ ተስፋ አድርጋለሁ” ብለዋል።
ኢትዮጵያ የሕዳሴ ግድብ የውሃ ሙሌት በምንም ዓይነት መልኩ እንደማይራዘም ማስታወቋን ያነሱት ኦስማን ማርጋኒ፣ “የኢትዮጵያ መልዕክት ግድቡን ለመሙላት የተያዘው ጊዜ እንደተጠበቀ መሆኑን በመረዳት ይህ ጉዳይ የድርድሩ አካል እንዳይሆን ማስገንዘብ ነው” ብለዋል፡፡ የግድቡ መገንባት እና የውሃ ሙሌቱ የድርድር አካል እንደማይሆኑ ኢትዮጵያ የያዘችውን አቋም በተግባር እያሳየች መሆኑን የገለጹት ተንታኙ ፣ ይህም ሦስቱ ሀገራት ሊስማሙ የሚችሉባቸውን ሌሎች አማራጮች መፈለግ እንዳለባቸው የሚያሳይ እንደሆነ ተናገረዋል።
ግድቡ ለሱዳን እና ለግብፅም ጥቅም እንዳለው ኢትዮጵያ በተደጋጋሚ መግለጿን በመጥቀስ ፣ ምን አይነት ጉዳት እና ጥቅም ሊኖረው ይችላል በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄም፣ “ግድቡ አሁን በመሬት ላይ እውን ሆኗል፤ የጥቅም እና ጉዳት ጉዳይ ግድቡ ከመገንባቱ በፊት መነሳት የነበረበትና አሁን ያለቀለት ነገር ነው” በማለት መልሰዋል።
በሶስቱ ሀገራት መካከል ከድርድር ጋር ተያይዞ የተፈጠሩ “አለመግባባቶች ከግድቡ ጥቅሞች እና ጉዳቶች ጋር አይገናኙም” ሲሉም ተናግረዋል።
ሱዳን ከድርድሩ የምትፈልገው “ግድቡ ወደ ስራ በሚገባበት ጊዜ ከሚኖረው አስተዳደር እና ከመረጃ ልውውጥ ጋር የተያያዙ ናቸው” ያሉት ኦስማን ማርጋኒ ግብፅ ደግሞ “ህጋዊ ስምምነት እና ዓለም አቀፍ ዋስትና እንዲኖር ነው ከድርድሩ የምትፈልገው” ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ ተመድ፣ የአውሮፓ ህብረት፣ አሜሪካና የአፍሪካ ሕብረት በአደራዳሪነት ይግቡ የሚለውን ሀሳብ ውድቅ ካደረገች በኋላ ሱዳን አዲስ የዲፕሎማሲ ዘዴን ትጠቀም ይሆን? በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄ ሲመልሱ “እኔ አይመስለኝም” ነው ያሉት፡፡ ለዚህም ምክንያት “ካርቱም የጥንቃቄ እርምጃዎችን ጀምራለች” የሚል ነው፡፡ የድርድሩ ጉዳይ እንደማያዛልቃት የተረዳችው ሱዳን አሁን ላይ ከሕዳሴ ግድብ ጋር በተያያዘ “ወደ ሁለተኛ አማራጭ እየተሸጋገረች ነው” ሲሉም ተናግረዋል።
በዚህ አማራጭም ሱዳን የውሃ ብክነትን ለማካካስ የጥንቃቄ እርምጃዎችን መውሰድ እና ውሃ ቀድማ የመያዝ እቅድ እንደምትከተልም አስታውቀዋል።