የጸጥታው ምክር ቤት በመካከለኛው ምስራቅ ቀጠናዊ ጦርነት የመቀስቀስ እድሉ ከፍተኛ ነው ሲል አስጠነቀቀ
በምክር ቤቱ ቻይና፣ ሩስያ፣ ኢራንና አልጄርያ የሀማስ የፖለቲካ ቢሮ ሀላፊ ግድያን አውግዘዋል
በሰአታት ልዩነት ውስጥ የሂዝቦላና የሀማስ ከፍተኛ አመራሮች ግድያን ተከትሎ ሊኖር የሚችለው የአጸፋ ምላሽ ቀጠናዊ ግጭትን ሊቀሰቀስ እንደሚችል ተሰግቷል
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት በመካከለኛው ምስራቅ ሁሉን አቀፍ ቀጠናዊ ጦርነት የመቀስቀስ እድሉ ከመቼውም ጊዜ በላይ ማሻቀቡን አስታወቀ፡፡
ምክር ቤቱ ትላንት ባደረገው ስብስባ በቀጠናው ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ የመከረ ሲሆን የጋዛው ጦርነት ወደ ቀጠናዊ ግጭት ሊያድግ እንደሚችል አስጠንቅቋል፡፡
ከ24 ሰአታት ባነሰ ልዩነት ውስጥ በቤሩት እና ተሄራን የሀማስ እና የሂዝቦላ ከፍተኛ አመራሮች ግድያ ግጭቱን ሊያባብሱ ከሚችሉ አሁናዊ ጉዳዮች መካከል ዋነኛው ነው፡፡
የጸጥታው ምክር ቤት የአመራሮቹን ግድያ ተከትሎ ሂዝቦላ እና ኢራን በእስራኤል ላይ የአጸፋ ጥቃት የሚሰነዝሩ ከሆነ ነገሮች ከቁጥጥር ውጭ ሊሆኑ እንደሚችል አስጠንቅቋል፡፡
ኢራን የሀማስ የፖለቲካ ቢሮ ሀላፊ እስማኤል ሀኒየህ በዋና ከተማዋ ቴህራን በተፈጸመባቸው የሚሳኤል ጥቃት መገደላቸው ተከትሎ በእስራኤል ላይ ከፍተኛ የበቀል እርምጃ እንደምትወስድ ዝታለች፡፡
የኢራን ሀይማኖታዊ መሪ አያቶላ አሊ ሀሚኒ በድንበር ክልላችን ውስጥ ለተከሰተው ወንጀል በእጥፍ አባዝተን ምላሽ እንሰጣለን ብለዋል በዚህም በቀጠናው ያለው ውጥረት ተባብሶ ይገኛል፡፡
ዛቻውን ተከትሎ በትላንትናው አለት በቴሌቪዝን ብቅ ብለው መልዕክት ያስተላለፉት የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚንስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ፤ ሀገራቸው ከብዙ አቅጣጫ ዛቻ እየተሰነዘረባት እንደሚገኝ ፣ ዜጎችም በአንድነት እንዲቆሙ ጠይቀው፤ ከየትኛውም አካል ለሚሰነዘረው ጥቃት ተመጣጣኝ ምላሽ ለመሰጠት በቂ ዝግጅት መደረጉን አስታውቀዋል፡፡
የተመድ የጸጥታው ምክር ቤት ባደረገው ስብሰባ ግጭቱ ወደ ከፋ ሁኔታ ከመቀየሩ በፊት አለም አቀፉ ማህበረሰብ ዲፕሎማሲያዊ ጫናውን እንዲያበረታ ጠይቋል፡፡
ቻይና ፣ ሩስያ ፣ ኢራን አልጄርያ እና ሌሎችም ሀገራት የእስማኤል ሀኒየህ ግድያን ሲያወግዙ አሜሪካ ፣ ብሪታንያ እና ፈረንሳይ በቀጠናው ለሚገኝው አለመረጋጋት ኢራን ለታጣቂዎች የምታደርገው ድጋፍ ምከንያት ነው ሲሉ ወቅሰዋል፡፡
በተመድ የቻይና አምባሳደር በበኩላቸው የጋዛውን ጦርነት ለማስቆም የተደረጉ ሙከራዎች ውጤታማ አለመሆናቸው ውጥረቱ እንዲባባስ አድርጓል ተጽእኖ ፈጣሪ ሀገራት ጦርነቱን ለማስቆም ያደረጉት ጥረትም በቂ አይደለም ብለዋል፡፡
እስራኤል እና ፍልስጤም የሁለት ሀገርነት መፍትሄን ተግባራዊ አድርጎ ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን በጋዛ የሚደረገው ጦርነት በፍጥነት መቆም አለበት ያሉት ደግሞ በተመድ የብሪታንያ አምባሳደር ናቸው፡፡
በትላንቱ ጉባኤ በምክትል አምባሳደሯ የተወከለችው አሜሪካ በበኩሏ በኢራን ላይ ተጽእኖ መፍጠር የሚችሉ ሀገራት በቀጠናው የምታካሂደውን የእጅ አዙር ጦርነት እንድታቆም ሀላፊነታቸውን እንዲወጡ ጠይቃለች፡፡