ኢራን በእስራኤል ላይ ጥቃት ካደረሰች በኋላ በመካከለኛው ምስራቅ የበረራ መስተጓጎል አጋጠመ
ኢራን ያስወነጨፈቻቸው ሚሳይሎች እና ድሮኖች በእስራኤል ሚሳይል መከላከያ ስርአት ተመትተው መክሸፋቸው ተገልጿል

ባለፉት ሁለት ቀናት ቢያንስ ከ12 የሚሆኑ አየር መንገዶች በረራዎችን ሰርዘዋል፤ ወይም የበረራ መስመራቸውን ቀይረዋል
ኢራን በእስራኤል ላይ ጥቃት ካደረሰች በኋላ በመካከለኛው ምስራቅ የበረራ መስተጓጎል አጋጠመ።
አለምአቀፍ አየር መንገዶች ኢራን በእስራኤል ላይ የሚሳይል እና የድሮን ጥቃት ካደረሰች በኋላ ከአውሮፓ ወደ እስያ በረራ ለማድረግ የሚጠቀሙበት አማራጭ መስመር ጠቦ እክል ገጥሟቸዋል።
ኢራን በእስራኤል ላይ 300 ሚሳይሎች እና ድሮኖች ያስወነጨፈች ቢሆንም አብዛኞቹ በአሜሪካ በሚደገፈው የእስራኤል ሚሳይል መከላከያ ስርአት ተመትተው መክሸፋቸው ተገልጿል።
ይህ የእስራኤል እና ኢራን ግጭት የአቬሽን ኢንዱስትሪው ቀውስ ውስጥ እንዲገባ አድርጎታል።
ባለፉት ሁለት ቀናት የኳንታስ፣ የሉፍታንዛ፣ ዩናይትድ ኤየርላይንስ እና ኤየር ኢንዲያን ጨምሮ ቢያንስ ከ12 የሚሆኑ አየር መንገዶች በረራዎችን ሰርዘዋል፤ ወይም የበረራ መስመራቸውን ቀይረዋል።
የአየር ክልልን እና የአየር መንገድን እንደሚከታተለው ኦፒኤስ ግሩፕ ከሆነ ይህ የአየር መረራ መስተጓጎል የዓለም የንግድ ድርጅት ከተጠቃበት ከመስከረም 11፣2001 ወዲህ ከፍተኛው ነው።
የኢራን እና እስራኤል ግጭት፣ በዩክሬን-ሩሲያ እና በሀማስ -እስራኤል ጦርነቶች ምክንያት ለችግር የተጋለጠውን የበረራ ኢንዱስትሪ የበለጠ ይጎዳዋል ተብሏል።
ከእሲያ ወደ ከውሮፓ የሚጓዙ አየርመንገዶች የኢራንን የአየር ክልል የሚጠቀሙ የነበረ ሲሆን አሁን ላይ ሁለት አማራጮችን ብቻ ለመጠቀም ይገደዳሉ። በቱርክ በኩል ወይም በግብጽ እና በሳኡዲ አረቢያ በኩል የመብረረ አማራጭ ይኖራቸዋል።
እስራኤል በትናንትናው እለት ከመክፈቷ በፊት ቅዳሜ እለት የአየር ክልሏን ዝግ አድርጋው ነበር።
በረራ አቋርጠው የነበሩ በርካታ የመካከለኛው ምሰራቅ አየር መንገዶችም በትናንትናው እለት በረራ መጀመራቸውን አስታውቀዋል።
ኢራን በእስራኤል ላይ መጠነሰፊ ጥቃት የከፈተችው በሶሪያ የሚገኘውን ኢምባሲዋን አጥቅታለች በሚል ምክንያት ነው።
ኢራን በእስራኤል ላይ እወስደዋለሁ ስትለው የነበረውን የአየር ጥቃት ማብቃቷን ገልጻለች።
እስራኤል ጥቃቱን ማክሸፏን ከመግለጽ ውጭ ለዚህ ጥቃት የአጸፋ መልስ ስለመስጠት ያለችው ነገር የለም።