ሃማስና ፋታህ ለ17 አመታት የዘለቀውን ልዩነታቸውን በእርቅ መፍታታቸው ተነገረ
14 የፍልስጤም ተቀናቃኝ ሃይሎች በቻይና አደራዳሪነት ለሶስት ቀናት ያደረጉት ንግግር ተጠናቆ ስምምነት ተፈራርመዋል
የፍልስጤም ተቀናቃኝ ሃይሎች ጋዛን ከጦርነቱ በኋላ የሚያስተዳድር ጊዜያዊ የሽግግር መንግስት ለማቋቋም ተስማምተዋል ተብሏል
ሃማስ እና ፋታህ የ17 አመታት ክፍፍላቸውን በማቆም ለፍልስጤም አንድነት በጋራ ለመስራት ተስማሙ።
የሁለቱ ተቀናቃኞችን ጨምሮ የ14 የፍልስጤም የፖለቲካ ሃይሎች ተወካዮች በቤጂንግ ሲያደርጉት የቆዩት የእርቅ ንግግርና ድርድር መጠናቀቁን ሲጂቲኤን ዘግቧል።
የቻይናው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋንግ ይ በተገኙበትም ልዩነታቸውን በማጥበብ ለፍልስጤም አንድነት በጋራ ለመስራት በመስማማት “የቤጂንግ ስምምነት”ን ፈርመዋል ተብሏል።
ሃማስና ፋታህ ባለፈው ሚያዚያ ወር በቻይና ንግግር ማድረግ መጀመራቸው የሚታወስ ሲሆን፥ የፋታህ መሪው ማህሙድ አባስ በቅርቡ በጋዛ ለቀጠለው ጦርነት ሃማስን ተጠያቂ ማድረጋቸው ንግግሩን ያውካል ቢባልም በዛሬው እለት ከስምምነት ደርሰዋል።
ለሶስት ቀናት ከተካሄደው ንግግር በኋላ “የቤጂንግ ስምምነት” መፈረሙን ያደነቁት የቻይናው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋንግ ይ፥ የፍልስጤም ተቀናቃኝ ሃይሎች ጋዛን ከጦርነቱ በኋላ የሚያስተዳድር ጊዜያዊ የሽግግር መንግስት ለማቋቋም ከስምምነት መድረሳቸውን ተናግረዋል።
ለእስራኤል ነጻ ሀገርነት እውቅና መስጠት የማይፈልገውና በስድስት ቀናቱ ጦርነት በእስራኤል በሃይል የተያዙ ቦታዎች ተለቀው ነጻዋ ፍልስጤም ትመሰረታለች የሚለው ሃማስ ከእስራኤል ጋር የሰላም ስምምነት ከተፈራረመው የማህሙድ አባሱ ፋታህ ጋር ግንኙነቱ የሻከረ ነው።
በተለይ በፈረንጆቹ 2006 በተካሄደው ምርጫ ሃማስ ማሸነፉን ተከትሎም ዌስትባንክን ከሚያስተዳድረውና ፋታህ ከተቆጣጠረው የፍልስጤም አስተዳደር ጋር ልዩነቱ መስፋቱ ይታወሳል።
ሁለቱ ቡድኖች ተከታታይ ድርድር አድርገው የአንድነት መንግስት ለመመስረት መስማማታቸውም አይዘነጋም።
ስምምነቱ ሃማስ የፍልስጤም አስተዳደር ከእስራኤል ጋር የደረሰውን የሰላም ስምምነት እንዲያከብር የሚያደርግ ቢሆንም ለእስራኤል ሉአላዊ ሀገርነት እውቅና ያልሰጠበት በመሆኑ እስራኤልና አሜሪካ የአንድነት መንግስቱን እውቅና አንሰጠውም ብለው ኢኮኖሚያዊ ማዕቀቦችን ጥለው ነበር።
ይህም የሃማስና ፋታህ የአንድነት መንግስት በአጭር ጊዜ እንዲፈርስና ግጭት እንዲቀሰቀስ ምክንያት መሆኑ ይታወሳል።
እስራኤልና ምዕራባውያን አጋሮቿ ሃማስን በሽብርተኝነት በመፈረጅ ዌስትባንክን ለሚያስተዳድረው ፋታህ ደግሞ አለማቀፍ እውቅና በመስጠት የፍልስጤም የነጻነት ትግልን በሁለት ጎራ ከፍለውት ነበር።
በቻይና አደራዳሪነት የተደረሰው ስምምነት ተፈጻሚ መሆን ከቻለ ግን ሁለቱም ሀይሎች ለአንድ አለማ በጋራ በመታገል የፍልስጤምን ነጻነት በአጭር ጊዜ ማረጋገጥ እንደሚቻል ይገመታል።