ሐማስ ለሀኒየህ ግድያ ቴልአቪቭን ተጠያቂ ሲያደርግ እስራኤል ግን ግድያው እኔን አይመለከትም ብላለች
አሜሪካ በሐማሱ መሪ እስማኤል ሀኒየህ ግድያ ላይ እጄ የለበትም አለች።
ከ10 ወራት በፊት የተጀመረው የእስራኤል- ሐማስ ጦርነት አሁንም እንደቀጠለ ሲሆን አሁንም የእስራኤል ጦር የሐማስ አመራሮችን በፍልስጤም እና በሌሎች ሀገራት ኢላማ አድርጓል፡፡
የሐማስ የፖለቲካ ቢሮ ሀላፊ እስማኤል ሀኒየህ በኢራን መዲና ቴህራን በተፈጸመባቸው ጥቃት መገደላቸው ተገልጿል፡፡
ሐማስ ባወጣው መግለጫ እስማኤል ሀኒየህ በቴህራን በመኖሪያ ቤታቸው እያሉ በእስራኤል ጥቃት መገደላቸውን ያስታወቀ ሲሆን ግድያው እንዴት እንደተፈጸመ ምርመራ በመደረግ ላይ ነው ተብሏል፡፡
የእስራኤል ቀኝ እጅ የምትባለው አሜሪካ በእስማኤል ሀኒየህ ግድያ ላይ ተሳትፎ እንደሌላት አስታውቃለች።
የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚንስትር አንቶኒ ብሊንከን እንዳሉት "በሀማስ የፖለቲካ ግድያ ዙሪያ ተሳትፎም ሆነ እውቅና የለንም" ብለዋል።
ሀኒየህ ለመጨረሻ ጊዜ በአካል የታዩት በቴጅራን በተካሄደው የኢራን ፕሬዝዳንት መሱድ ፔዜሽኪያን በዓለ ሲመት ላይ ሲሆን በቀጣይ በሚደረጉ ስራዎች ዙሪያ ለመምከር በሚል በቴህራን እንደቆዩም በመግለጫው ላይ ተጠቅሷል፡፡
እስማኤል ሀኒየህ በፈረንጆቹ 2021 ላይ በተካሄደ ምርጫ የሐማስ የፖለቲካ ቢሮ ተደርገው የተመረጡ ሲሆን እስከ 2025 ድረስ በሀላፊነት እንደሚቆዩ ይጠበቅ ነበር፡፡
እስራኤል የሐማስ መሪዎችን በጋዛ እና በሌሎች ሀገራት ኢላማ በማድረግ ለይ ስትሆን ከወራት በፊት የሐማስ ምክትል የፖለቲካ ቢሮ ሀላፊ ሳሌህ አል አሩሪን በሊባኖስ መግደሏ ይታወሳል።
ይሁንና እስራኤል በሀማሱ ግድያ እንደማይመለከታት ስሙ ያልተጠቀሰ አንድ ወታደራዊ አመራር ተናግሯል።
ካሳለፍነው ጥቅምት ወር ጀምሮ በጋዛ ከባድ የሰብዓዊ ውድመት መድረሱን የሚገልጸው ሐማስ እስካሁን ከ130 ሺህ በላይ ፍልስጤማዊያን በእስራኤል ጦር መገደላቸውን ገልጿል፡፡
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ግን የሟቾችን ቁጥር ከ38 ሺህ በላይ ደርሷል ያለ ሲሆን በእስራኤል በኩል ደግሞ 1 ሺህ 200 ንጹሃን በሐማስ ተገድለዋል ብሏል፡፡
እንዲሁም እስራኤል በደረሰችው ጥቃት ከ10 ሺህ በላይ ፍልስጤማዊያን እስካሁን ያሉበት አልታወቀም ተብሏል፡፡