ሐማስ በእስራኤል ላይ ጥቃት የሰነዘረባቸው የጦር መሳሪያዎች ምንጫቸው የት ነው?
ሐማስ ከ40 ዓመት በፊት የተጠቀመውን የውጊያ ስልት ዳግም ተግብሯል ተብሏል
የሐማስ ታጣቂዎች ከተራ ክላሽ ጀምሮ ያልታሰቡ አዳዲስ የጥቃት መንገዶችን መጠቀሙ ተገልጿል
ሐማስ በእስራኤል ላይ ጥቃት የሰነዘረባቸው የጦር መሳሪያዎች ምንጫቸው የት ነው?
ከአንድ ሳምንት በፊት ማለዳ ላይ ነበር የፍልስጤሙ ሐማስ በእስራኤል ላይ ድንገተኛ ጥቃት መክፈቱ የተገለጸው፡፡
እስራኤልን በጠላትነት የሚያየው ሐማስ በተዳጋጋሚ ጥቃት በማድረስ ቢታወቅም የአሁኑ ግን ለየት ያለ እና ያልተጠበቀ እንደሆነ ተገልጿል፡፡
የሀማስን ጥቃት ተከትሎ በርካታ ጥያቄዎች በመነሳት ላይ ሲሆኑ ከጥያቄዎቹ መካከልም ሐማስ ያለ ሌሎች እርዳታ ይህን ጥቃት ሊያደርስ አይችልም፣ በመረጃ ስለላው ታዋቂ የሆነው የእስራኤሉ ሞሳድ እንዴት አስቀድሞ ሳይደርስበት ቀረ እና ሌሎችም ይጠቀሳሉ፡፡
የጦርነቱ ተሳታፊዎች ሀማስ እና የእስራኤል ጦር ተንቀሳቃሽ ምስሎችን የለቀቁ ሲሆን እነዚህን ምስሎች በማየት ትንታኔዎች በመውጣት ላይ ናቸው፡፡
ሲኤን ኤን ወታደራዊ ባለሙያዎችን ዋቢ አድርጎ እንደዘገበው ከሆነ የሀማስ ዝግጅት ረጅም ጊዜ የፈጀ እና የበርካታ ሀገራት ድጋፍ የተደረገበት ነው፡፡
የሀማስ ታጣቂዊች በእስራኤል ላይ ባደረሱት ጥቃት ክላሽ፣ አልሞ መምቻ የሆኑ መሳሪያዎች፣ የእጅ ቦምብ፣ ሮኬት፣ ድሮን፣ ለፊልም ስራዎች የሚውሉ መንሸራተቻዎች እና ሌሎችንም የጦር መሳሪያዎችን ተጠቅመዋል ተብሏል፡፡
እስራኤል በጋዛ ላይ ስድስት ሺህ ቦምብ ማዝነቧን አስታወቀች
እንደ ስናይፐር አይነት ከርቀት አልሞ መምቻ የጦር መሳሪያ እና ክላሽኮቭ ወይም በተለምዶ ክላሽ የሚባሉት የጦር መሳሪያዎች ዳግም ለውጊያ እና በቀላሉ ለመተኮስ እንዲያመቹ ተብለው ማሻሻያ የተደረገባቸው እንደሆኑም እነዚህ ወታደራዊ ባለሙያዎች ተናግረዋል፡፡
ይሁንና ያረጁ የጦር መሳሪያዎች ጥቅም ላይ ውለዋል የተባለ ሲሆን ሀማስ እነዚህን የጦር መሳሪያዎች ከአፍጋኒስታን፣ ከሊቢያ፣ ቻይና፣ ሩሲያ፣ ኢራቅ እና ኢራን ያሰባሰባቸው ሊሆኑ እንደሚችሉም ተገልጿል፡፡
የሀማስ ታጣቂዎች የተጠቀሟቸው የእጅ ቦምቦች ውድ እና የበለጸጉ ሀገራት ሳይቀር እጥረት ያለባቸው አይነት ቦምቦች ናቸው የተባለ ሲሆን እንደዚህ አይነት የቡድን ጦር መሳሪያዎች በእርዳታ የተሰጡ የመሆን እድሉ ከፍተኛ ነው ተብሏል፡፡
ሌላኛው የሀማስ ታጣቂዎች የተጠቀሙት ሮኬት እና ድሮኖች ሲሆኑ እንደ ኢራን ያሉ ሀገራት ለሀማስ ካልተሰጡ በስተቀር ሐማስ በራሱ ሊያመርታቸው የሚችላቸው እንዳልሆኑ ባለሙያዎቹ ተናግረዋል፡፡
ሌላኛው እና ብዙዎችን ያስገረመው የሀማስ ታጣቂዎች የተጠቀሙት የማጥቂያ መንገድ በተለምዶ ለፊልም ስራዎች ይውሉ የነበሩ የአየር ላይ መንሳፈፊያዎች ናቸው፡፡
ሐማስ እነዚህን መሳሪያዎች ከ40 ዓመት በፊት ተጠቅሟቸው ነበር የተባለ ሲሆን በፈረንጆቹ 1980ዎቹ ላይ መንሳፈፊያዎቹን ተጠቅሞ በእስራኤል ወታደሮች ላይ ድንገተኛ ጥቃት ከፍቶ እንደነበር ተገልጿል፡፡
በአሁኑ የሀማስ ጥቃት ላይ በርካታ ሀገራት ከጀርባ ሆነው እንደረዱ የተጠረጠሩ ቢሆንም የኢራን ከዚህ ጥቃት ጀርባ ስለመኖሯ በይፋ እየተነገረ ይገኛል፡፡