አሜሪካ እና ታሊባን በታገደው ገንዘብ ዙሪያ ውይይት አድርገዋል
አሜሪካ በሽብር ትፈልገው ከነበረው የአፍጋኒስታን ወቅቱ አስተዳዳሪ ታሊባን ጋር መወያየቷን አስታወቀች፡፡
የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት እንደገለጸው ከሆነ ሁለቱ ወገኖች ውይይት ያደረጉት በኳታር መዲና ዶሃ ከተማ ነው፡፡ የአሜሪካና የአፍጋኒስታን መሪዎች ንግግር በሀገሪቱ በመሬት መንቀጥቀጥ ስለደረሰው ጉዳት እንደሆነ ተገልጿል፡፡
የአሜሪካ ባለስልጣናት ከወቅቱ የአፍጋኒስታን አስተዳደር ታሊባን ጋር የተገናኙት መጋቢት ላይ በተመሳሳይ በዶሃ ከተማ ነበር፡፡ ታሊባን አሜሪካ የያዘችውን የውጭ ምንዛሬ እንድትለቀው መንገድ እያፈላለገ መሆኑን ገልጿል፡፡ የአፍጋኒስታን አስተዳዳሪ ታሊባን ይህንን ተቀማጭ የውጭ ምንዛሬ አሁን በሀገሪቱ ለደረሰው የመሬት መንቀጥቀት አደጋ ተጎጅዎች ለማዋል ማሰቡንም ፍራንስ 24 ዘግቧል፡፡
ታሊባን በአሜሪካ ማዕቀብ የተጣለበትን ገንዘብ ብትሰጥ ለተጎጅ ሕዝብ እንደሚደርስ መተማመኛ ሰምጠት እንደሚችልም ገልጿል፡፡ የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ሰዎች ከታሊባን ተወካዮች ጋር ከተገናኙ በኋላ በአፍጋን ለደረሰው አደጋ ድጋፍ የሚሆን 55 ሚሊዮን ዶላር ለመስጠት መወሰናቸው ተገልጿል፡፡
አሜሪካ እንዳይንቀሳቀስ ስላደረገችው 3 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር ገንዘብ ጉዳይም ከታሊባን ተወካዮች ጋር መነጋገሯን ገልጻለች፡፡ አሜሪካ ለአፍጋኒታን ህዝብ ጥቅም ሲባል ገንዘቡን መጠቀም በሚቻልበት ጉዳይ ዙሪያ መነጋገሯን ነው የገለጸችው፡፡
በአፍጋኒስታን ባለፈው ሳምንት በሬክተር ሴኬል 5 ነጥብ 9 የተለካ የመሬት መንቀጥቀጥ መድረሱ ይታወሳል፡፡ በዚህ አደጋም 1000 ሰዎች መሞታቸውና በሺዎች የሚቆጠሩ ቤት አልባ መሆናቸው ይታወሳል፡፡