ታሊባን የአፍጋኒስታን ሴቶች “ከ72 ኪሎ ሜትር በላይ ብቻቸውን እንዳይጓዙ” አገደ
ሂዩማን ራይትስ ዎች “እገዳው ሴቶች ለእስር የሚዳርግ አደገኛ መመርያ ነው” ብሏል
ታሊባን ባለፈው ወር ሴቶች የቴሌቭዥን ድራማዎች ላይ እንዳይተውኑ የሚያስገድድ መመርያ ማውጣቱ ይታወሳል
ታሊባን በትራንስፖርት ረዥም ጉዞ ማድረግ የሚፈልጉ የአፍጋኒስታን ሴቶች አጠገባቸው የቤተሰብ አባል የሆነ ወንድ ከሌለ በስተቀር የትራንስፖርት አገልግሎት እንዳያገኙ አግዷል፡፡
አዲሱ እገዳ፤ታሊባን በትረ-ስልጣን ከጨበጠበት ካለፈው ወርሃ ነሃሴ ወዲህ ከባዱ መመርያ ነው ተብሏል፡፡
በአፍጋኒስታን መከላከያ ሚኒሰቴር እንደወጣ የተገለጸው አዲሱ መመርያ ሴቶች ወንድ ልጅ አብሮአቸው ከሌለ በስተቀረ ከ72 ኪሎ ሜትር በላይ መጓዝ እንደሌለባቸው የሚያዝዝ ነው፡፡
የትራንስፖርት ሰጪ አካላት ራሷን ያልሸፈነች ሴት እንዳያሳፍሩም የወጣው የመመርያ ሰነድ አስጠንቅቋል፡፡ከዚህም በተጨማሪ በመኪኖች ላይ ሙዚቃ መክፈት ተከልክሏል፡፡
የወጣው አዲሱ መመርያ ተከትሎም የሁለተኛ ደረጃ ሴት ተማሪዎች ከትምህርት ገበታቸው መስተጓጎላቻንና በርካታ ሴቶች ከስራ መታገዳቸው የፈረንሳዩ የዜና ወኪል/ኤ.ኤፍ.ፒ/ ዘግቧል፡፡
ሂዩማን ራይትስ ዎች በበኩሉ “አዲሱ እገዳ ሴቶች ለእስር የሚዳርግ አደገኛ መመርያ ነው” ብሎታል፡፡
በሂዩማን ራይትስ ዎች የሴቶች መብቶች አስተባባሪ ሄዘር ባር ጉዳዩን በማስመልከት ለAFP በሰጠቱት አስታየት "መመርያው የመንቀሳቀስ መብት የሚገድብ ከመሆኑ ባሻገር ሴቶች በቤት ውስጥ ሊገጥማቸው ከሚችል ጾታዊ ጥቃት የማምለጥ እድል የሚነፍግ ነው" ብሏል፡፡
የአሜሪካና የኔቶ ጥምር ኃይል አፍጋኒስታንን ለቆ መውጣጡ ተከትሎ ወደ ስልጣን የመጣው ታሊባን፤ አብዛኞቹ ሴቶች እቤት እንዲቆዩ እና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት እንዳይከታተሉ የሚያስገድድ መመርያ አውጥቶ ነበር፡፡
ታሊባን በሴቶች ላይ የጣለውን እገዳ የሴቶች ደህንነት እስኪረጋገጥ የተደነገገ "ጊዜያዊ" ነው ቢልም በበርካቶች ዘንዳ ተቃውሞ እየገጠመው ይገኛል።
ለጋሽ ሀገራትም ለታሊባን የሚያደረጉት የገንዘብ ድጋፍ ከመስጠታቸው በፊት የአፍጋኒስታን ሴቶች መብቶች እንዲከበሩ በመጠየቅ ላይ ናቸው፡፡
ታሊባን፡ ባለፈው ወር ሴቶች የቴሌቭዥን ድራማዎች ላይ እንዳይተውኑ እንዲሁም ሴት የቴሌቭዥን ዜና አቅራቢዎች ጸጉራቸው እንዲሸፍኑ የሚያስገድድ መመርያ ማውጣቱም የሚታወስ ነው፡፡
ታሊባን በ1990ዎቹ ሀገሪቱን ሲያስተዳደር በነበረበት ወቅት መሰል እገዳዎች በሴቶች ላይ ያደርግ እንደነበር ይታወቃል፡፡አፍጋኒስታን ፤ ቀደም ሲል ታገኝ የነበረውን እገዛ በመቋረጡ በከፍተኛ የሰብዓዊና ምጣኔ ሃብታዊ ቀውስ ውስጥ ተዝፍቃ የምትገኝ ሀገር ናት፡፡