ታሊባን፤ አሜሪካን እና የአውሮፓ ህብረትን አስጠነቀቀ
በአፍጋኒስታን ሰብዓዊ ተግባራትን ለመደገፍ ዋሸንግተን እና ብራሰልስ ዝግጁ መሆናቸውን አስታውቀዋል
ታሊባን በአፍጋኒስታን ላይ የተጣሉ ማዕቀቦችን በማስመልከት ነው ያስጠነቀቀው
አፍጋኒስታንን እየመራ ያለው ታሊባን አሜሪካ እና የአውሮፓ ህብረት የጣሏቸውን ማዕቀቦች የማያነሱ ከሆነ በርካቶች ሊሰደዱ ይችላሉ ሲል አስጠነቀቀ፡፡
ጊዜያዊው የአፍጋኒስታን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አሚር ከሃን ሙታቂ በዶሃ በነበረ ውይይት ላይ ከምዕራባውያን ዲፕሎማቶች ጋር መነጋገራቸው ተሰምቷል፡፡ በዚህ ውይይትም የአፍጋኒስታን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር፤ ለሌሎች ፍላጎት ሲባል የአፍጋኒስታንን መንግስት ማዳከም ከባድ ችግር ሊያስከትል እንደሚችል ገልጸዋል ተብሏል፡፡
“አፍጋኒስታን አሁን ነጻ እና ሉዓላዊ ሀገር ነች”- ታሊባን
አሁን ላይ ካቡልን ለማዳከም በማሰብ የተጣሉት ማዕቀቦች የዓለምን የጸጥታ ዘርፍ ከመጉዳትም ባለፈ በኢኮኖሚ ችግር ምክንያት በርካታ ዜጎች ሀገራቸውን ለቀው እንዲሰደዱ ሊያደርጉ ይችላሉ ነው የተባለው፡፡
በማዕቀቦቹ ምክንያት በአፍጋኒስታን ባንኮች ገንዘብ እንደቸገራቸውና እና ሰራተኞችም ክፍያ እንዳልተከፈላቸውም እየተገለጸ ነው፡፡
ዶሃ በተደረገው ውይይት የአፍጋን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር፤ ሀገራት በታሊባን ላይ ያላቸውን ቂምና ማዕቀብ እንዲያበቃ በማድረግ ባንኮች ስራቸውን ጤናማ በሆነ መንገድ እንዲሰሩ ጠይቀዋል፡፡ ማዕቀቦቹ የሚነሱ ከሆነ የዕርዳታ ድርጅቶች እና የመንግስት ሰራተኞች ክፍያን መፈጸም እንደሚቻልም ነው የገለጹት፡፡
የአውሮፓ ሀገራት የአፍጋን ኢኮኖሚ የሚወድቅ ከሆነ በርካታ ስደተኞች ሀገሪቷን ለቀው ሊወጡ እንደሚችሉ ስጋቱን ገልጿል፡፡ ይህም የአፍጋን ዜጎች ጎረቤት ወደሆኑት ፓኪስታንንና ኢራን እንዲሁም ወደ አውሮፓ ሀገሮች ድንበሮች እንዲሰደዱ ሊያደርጋቸው ይችላል ነው የተባለው፡፡
“የአሜሪካ የአፍጋኒስታን ቆይታ በአሳዛኝ ሁኔታ ነው የተቋጨው”- ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን
አሜሪካና የአውሮፓ ሕብረት በአፍጋኒስታን ሰብዓዊ ተግባራትን ለመደገፍ ዝግጁ መሆናቸውን አስታውቀዋል፡፡ ዋሸንግተንና ብራሰልስ ፤ታሊባንን ለመደገፍ ቡድኑ የሰብዓዊ መብቶችን በተለይም የሴቶችን መብቶች ያከብራል ወይ የሚለውን በጥንቃቄ ማየት እንደሚገባ ማሳወቃቸውን ዴይሊ ሜይል ጽፏል፡፡