አሜሪካ ከኢራን ጋር ለመደራደር ስትል ማእቀብ እንደማታነሳ አስታወቀች
አሜሪካ ከኢራን ጋር ለመደራደር ስትል በኢራን ላይ የጣለችዉን ማእቀብ እንደማታነሳ ፕሬዘዳንት ዶናልድ ትራምፕ ማስታወቃቸውን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
ፕሬዘዳንቱ ይህን ያሉት የኢራን የዉጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሞሀማድ ጃቫድ ዛሪፍ ከፎክስ ኒውስ ጋር ባደረጉት ቆይታ ከአሜሪካ ጋር መደራደር እንፈልጋለን፤ ነገርግን ማእቀቡ እንዲነሳ እንፈልጋለን ማለታቸውን ተከትሎ ነው፡፡
የኢራን የዉጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አሜሪካ ማእቀቧን ካነሳች ኢራን አሁንም ቢሆን ለድርድር በሯ ክፍት እንደሆነ በትዉይተር ገጻቸው ገልጸዋል፡፡ ሚኒስትሩ ፕሬዘዳንት ትራምፕ የዉጭ ጉዳይ ፖሊሲ ዉሳኔ ሲወስኑ እዉነታን ከግምት ማስገባት እንዳለባቸው ገልጸዋል፡፡
ባለፈው ታህሳስ ወር መጨረሻ በአሜሪካ ወታደራዊ ዘመቻ የኢራኑ ጄነራል ቃሲም ሱሌማኒ በኢራቅ ምድር ከተገደሉ በኋላ በአሜሪካና በኢራን መካከል ያለው ዉጥረት ብሏል፡፡
ኢራንም ይህን ተከትሎ በኢራቅ ሰፍረው በሚገኙ የአሜሪካ ወታደሮች ላይ ሚሳል በመተኮስ አጸፋዊ እርምጃ ወሰዳለች፡፡