44 ቢሊየን ዶላር በማጭበርበር የተከሰሱት ቬትናማዊት ቢሊየነር በሞት እንዲቀጡ ተወሰነባቸው
የ67 አመቷ ቢሊየነር ትሩኦንግ ማይ 2 ሺህ 700 ምስክሮችና ከ5 ሺህ 400 ኪሎግራም በላይ የሚመዝን ማስረጃ ቀርቦባቸው ነው ጥፋተኛ የተባሉት
የመዋቢያ እቃ በመሸጥ ንግድ የጀመሩት ትሩኦንግ የሀገሪቱን ንግድ ባንክ እንዳሻቸው ሲዘውሩት ነበር ተብሏል
በቬትናም ከባድ የባንክ ማጭበርበር ፈጽመዋል የተባሉት ቢሊየነር የሞት ቅጣት ተላለፈባቸው።
ትሩኦንግ ማይ ላን የተባሉት ቢሊየነር ባለፉት 11 አመታት የሀገሪቱን ትልቅ ባንክ ሲዘርፉ ቆይተዋል በሚል በቀረበባቸው ክስ ነው ቅጣቱ የተላለፈባቸው።
በሆቺ ሚኒ ከተማ የሚገኘው ፍርድ ቤት በቬትናም ከገንዘብ ማጭበርበር ጋር በተገናኘ የመጀመሪያ የሞት ቅጣት ውሳኔውን በዛሬው እለት አሳልፏል።
የ67 አመቷ ቢሊየነር “ሳይጎን” ከተሰኘው ንግድ ባንክ 44 ቢሊየን ዶላር በማጭበርበር ወስደዋል የሚል ክስ ቀርቦባቸዋል።
ትሩኦንግ ከወሰዱት ብድር ውስጥ 27 ቢሊየን ዶላሩን እንዲመልሱ ብይን ቢሰጥም አቃቤ ህግ መመለስ እንደማይችል በማረጋገጡ የሞት ቅጣት ተላልፎባቸዋል ነው የተባለው።
የሞት ፍርዱ ቢሊየነሯ በተለያዩ ሚስጢራዊ ኩባንያዎቻቸው የደበቁትን ሀብት በመጠቀም ብድራቸውን እንዲመልሱ ያበረታታል ተብሎ ታምኖበታል።
የቬትናም ባለስልጣናት ባልተለመደ መልኩ ስለቢሊየነሯ ክስ ዝርዝር መረጃ መስጠታቸውን የጠቀሰው ቢቢሲ፥ በክስ ሂደቱ 10 አቃቤ ህጎች እና 200 ጠበቆች መሳተፋቸው መገለጹን ዘግቧል።
2 ሺህ 700 ምስክሮች ቃላቸውን እንዲሰጡ የጥሪ ወረቀት እንደደረሳቸውና ከ5 ሺህ 400 ኪሎግራም በላይ የሚመዝኑ ማስረጃዎች በ104 ሳጥኖች መቅረባቸውም ተጠቁሟል።
በቬትናም ታይቶ አይታወቅም በተባለው ግዙፍ የፍርድ ሂደት ከቢሊየነሯ ጋር 85 ሰዎችም ክስ ቀርቦባቸዋል ተብሏል።
የቬትናም ኮሚኒስት ፓርቲ ዋና ጸሀፊ ንጉየን ትሮንግ ሙስና የፓርቲያችን ህልውና አደጋ ነው ብለው ከ2016 ጀምሮ የጸረ ሙስና ዘመቻ መጀመራቸው ይታወሳል።
ዘመቻው ሁለት ፕሬዝዳንቶች እና ሁለት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሮች ከስልጣን እንዲለቁ እንዲሁም በመቶዎች የሚቆጠሩ ባለስልጣናት በዲሲፕሊን ቅጣትና በእስር እንዲቀጡ ማድረጉ ተገልጿል።
የቬትናም ቀዳሚዋ ሴት ቢሊየነርም ይሄው የዋና ጸሃፊው ዘመቻ ዘብጥያ ወርውሯቸው የሞት ቅጣት ተላልፎባቸዋል።
ሁሉም መሬት በመንግስት በሚተዳደርባት ቬትናም ለሆቴልም ሆነ ለፋብሪካ መሬት ለማግኘት ከባለስልጣናት ጋር ልዩ ግንኙነት መመስረት ግድ ነበር። ይህም እድገቷ ፈጣን የነበረውን ሀገር ሙስና እንዲስፋፋባት አድርጓል።
ሁኔታው የሀገሪቱ መንግስት በፈረንጆቹ 1986 የኢኮኖሚ ማሻሻያ እንዲያደርግ ሲያስገድደው የመዋቢያ እቃዎችን በመሸጥ የንግዱን አለም የተቀላቀሉት ትሩኦንግ ማይ ላን መሬት በስፋት መግዛት ጀመሩ።
በሆቺ ሚኒ የታዋቂ ሁቴሎች ባለቤት መሆን የቻሉት ትሩኦንግ ሀብት በሀብት እየደረቡ ሲሄዱም ጊዜ አልወሰደባቸውም።
የሳይጎን ንግድ ባንክ ግን ዋነኛ መወጣጫቸው ነበር ይላል የቀረበባቸው ክስ።
የቬትናም ህግ ማንኛውም ግለሰብ በየትኛውም ባንክ ውስጥ ከ5 በመቶ በላይ ድርሻ እንዳይረው ቢከለክልም ቢሊየነሯ ግን በኩባንያዎቻቸው ስም ባንኩን የግል ንብረታቸው አድርገውታል ነው የተባለው።
የባንኩን ስራ አስኪያጆች እንዳሻቸው እየሾሙ ስም እንጂ ሰራተኛም ሆነ ስራ ለሌላቸው “ሼል ኩባንያዎች” በቢሊየን ዶላር ብድር እንዲፈቅዱ ሲያደርጉ እንደነበር ክሱ ያስረዳል። ባንኩ ከለቀቀው ብድር ውስጥ 93 በመቶው ለትሩኦንግ ማይ ላን ኩባንያዎች የቀረበ እንደነበርም ተገልጿል።
ከ2019 ጀምሮ ለሶስት ዓመታት ሾፌራቸው 108 ትሪሊየን የቬትናም ዶንግ (ከ4 ቢሊዮን ዶላር በላይ) በጥሬ ገንዘብ እንዲያወጣ አድርገው በምድር ቤታቸው ማከማቸታቸው የተገለጸ ሲሆን፥ የተከማቸው የገንዘብ ኖት ሁለት ኩንታል ይመዝናል ተብሏል።