“በይሆናል ግምታዊ ሁኔታ እንዳይመረጡ በማሰብ የታሰሩ ፖለቲከኞችን በእጩነት አልመዘገብንም”- ብርቱካን ሚደቅሳ
በእስር ላይ የሚገኙ ፖለቲከኞች በእጩነት ከመመዝገብ ሊከለከሉ የሚችሉበት የህግ አግባብ እንደሌለ ሰብሳቢዋ ገልጸዋል
ቦርዱ እስረኞቹ ቢያሸንፉ እንዲፈቱ ሊጠይቅ የሚችልበት የህግ አግባብ የለም
በእስር ላይ የሚገኙ የፓለቲካ ፓርቲ አባላትና አመራሮችን በይሆናል እንዳይመረጡ በማሰብ በእጩነት አለመመዝገቡን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አስታወቀ፡፡
ቦርዱ ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ በፓርቲዎች ተደጋጋሚ ጥያቄዎች እንደቀረቡለት አስታውቋል፡፡
የምርጫ ዓላማ የዜጎች ድምጽ የስልጣን ውክልና እንዲኖረው ማድረግ ነው ያሉት የቦርዱ ሰብሳቢ ወ/ሪት ብርቱካን ሚደቅሳ “እስር ቤት ያሉ ሰዎችን በእጩነት ብንመዘግብ የዓላማው መሳካት ብዙ ችግሮች ይገጥሙታል” ሲሉ ተናግረዋል ትናንት በነበራቸው ጋዜጣዊ መግለጫ፡፡
በእጩነት የተመዘገቡ እስረኞች ወጥተው ሊቀሰቅሱ እና ቢያሸንፉ ምክር ቤት ሊያቋቁሙ የሚችሉበት “የህግ አግባብ”ላይኖር እንደሚችልም ነው ሰብሳቢዋ የተናገሩት፡፡
“ፓርላማ ወይም የክልል ምክር ቤት ማቋቋሚያ ቀን ተፈተው ሊመጡ መቻላቸውን ቦርዱ እርግጠኛ ሊሆን አይችልም፤ ወይም ደግሞ ስለተመረጡ ይፈቱ የሚባልበት ቢያንስ በህግ የምንጠይቅበት አግባብ የለም” ሲሉም አስቀምጠዋል፡፡
ወ/ሪት ብርቱካን “መራጮች ተፈቶ/ተፈታ ፓርላማ ይገባልኝ ይሆናል በሚል ግምታዊ ሁኔታ ላይ ተመስርተው ነው የሚመርጡት ማለት ነው” ሲሉ የሚያስቀምጡም ሲሆን ሁኔታው ግራ አጋቢና በስተመጨረሻም ኃላፊነትን ለመውሰድ የማያስችል መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ቦርዱ ሰዎቹ ባይገኙ ወይም እዛው እስር ቤት ቢቆዩ መፍትሄ የሚሰጥበት “ምንም ዐይነት አግባብ” እንደሌለም ነው “እንደገና ምርጫ ልናደርግ ነው ወይስ ሁለተኛ የወጣውን ልናስገባ?” ሲሉ የሚያጠይቁት ሰብሳቢዋ የሚናገሩት፡፡
“ህጋችን በአጠቃላይ ለእንዲህ አይነቱ ጉዳይ ምላሽ የለውም”ም ብለዋል፡፡
ወ/ሪት ብርቱካን መብታቸው በህግ ባይከለከልና ባይገደብም ቦርዱ አሁን ባለው ዐቅም እስር ቤት ያሉ ዜጎችን እና ዳያስፖራ ኢትዮጵያውያንን እጩም መራጭም አድርጎ እንደማይዘግብ አስታውሰዋል፡፡