ከታጣቂ ኃይሎች ጋር በውጭ ሀገራት ለመገናኘት ሀሳብ አቅርበናል -ፕሮፌሰር መስፍን
የኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር መሳርያ አግበው ከመንግስት ጋር እየተፋለሙ ያሉ አካላትን ለማሳተፍ የተለያዩ ጥረቶች ተደርገዋል ብለዋል
ኮሚሽኑ በቀሩት ወራት ስራዎችን ለማጠናቀቅ እየሰራ እንደሚገኝ እና የሰራ ጊዜው እንዲራዘም እንደማይፈልግም ዋና ኮሚሽነሩ ግልጸዋል
ከዘመናዊ የሀገሪቱ ታሪክ ጀምሮ ባለፉት 50 እና 60 አመታት ለግጭት እና ንትርክ መንስኤ የሆኑ ጉዳዮች ላይ መግባባት የሚያስችል ብሔራዊ ምክክር ለማድረግ የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በ2014 መመስረቱ ይታወሳል፡፡
11 ኮሚሽነሮችን ይዞ ለሶስት አመታት የተቋቋመው ኮሚሽን የተለያዩ አላማዎችን አንግበው የፖለቲካ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች መሰረት አድርገው ላለመግባባት ምክንያት ጫፍ እና ጫፍ ያሉ አጅነዳዎችን ማቀራረብ ዋነኛ አላማው እንደሆነ ይነገራል፡፡
ከምስረታው ጀምሮ የገለልተኛነት እና የአሳታፊነት ጥያቄዎችን ጨምሮ የተለያዩ የመወዛገቢያ አጀንዳዎች ያልተለዩት ኮሚሽኑ የስራ ጊዜው ሊጠናቀቅ በጣት የሚቆጠሩ ወራቶች ቀርተውታል፡፡
የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ ኮሚሽኑ የውይይት ጽንሰ ሐሳብን የበለጠ ለመረዳት በሚያስችሉ፣ የአደረጃጀትና ስትራቴጂካዊ ጉዳዮችን የሚዳስሱ ሰነዶችን ማዘጋጀቱን ለአል ዐይን አማርኛ ተናግረዋል።
ፕሮፌሰር መስፍን “በዋናነት አጀንዳ ቀረፃ፣ ውይይትና ከውይይት የሚገኙ ምክረ ሐሳቦች እንዲተገበሩ ክትትል ማድረግ ላይ ትኩረት እናደርጋለን፤ አሁን የምንገኝበት ሁኔታ በወረዳ፣ ክልል እና በፌደራል ደረጃ አጀንዳ መሰብሰብ እና ለሀገራዊ ምክከር ጉባኤው ሰዎችን የማስመረጥ ሰራ እየሰራን ነው ፤ጋምቤላ ፣ ቤንሻንጉል ፣ ሀረሪ ፣ ሲዳማ አፋር ፣ አዲስአበባ ፣ ድሬዳዋ ፣ ማዕከላዊ ኢትዮጵያ እና ሶማሌ ክልል የአጀንዳ ማሰባሰብ ስራዎችን ጨርሰናል” ብለዋል፡፡
በውጭ ሀገራት የሚገኙ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ በቀሪ ክልሎችም ኮሚሽኑ የተሳታፊ ልየታ እና የአጀንዳ ማሰባሰብ ስራዎችን እያከናወነ እንደሆነ የገለጹት ዋና ኮሚሽነሩ፤ በአማራ እና ትግራይ ክልል ካለው ነባራዊ ሁኔታ አንጻር በሌሎች የሀገሪቱ አካባቢዎች ልክ ስራዎችን ለመስራት መቸገሩን ተናግረዋል።
ፕሮፌሰር መስፍን “አማራ ክልልን በተመለከተ በክልሉ አንጻራዊ ሰላም እንዲሰፍን እና መንግስት እና ታጣቂዎች ወደ ድርደር የሚመጡበትን እና የክልሉን ነዋሪዎች ሀሳብ ለማካተት እንዲያግዝ ኢንፎርማል በሆነ መንገድ እያሳሰብን እንገኛለን፡፡
ትግራይ ክልል በአመራር ደረጃ ኮሚሽኑ ስራ እንዲጀምር የፍቃደኝነት ችግር የለም። ነገር ግን ክልሉ በተፈናቃዮች ጉዳይ፣ አሁን ከሚገኝበት የፖለቲካ ሁኔታ እና ከሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ጋር በተገናኘ ጥያቄ አለው፤ እሱን በቅርበት ለመፍታት እና በቶሎ ስራ እንድንጀምር ከክልሉ አመራሮች ጋር እየተነጋገርን ነው” ብለዋል።
በትግራይ ክልል ተሳታፊ ልየታ እና አጀንዳ የመሰባሰብ ስራዎችን ለመስራት የጊዜዊ አስተዳደሩን ይሁንታ ነው የምንጠብቀው የሚሉት ኮሚሽነሩ እርሱን በቀሩት ወራት ለማሳካት ከአስተዳደሩ ጋር ጠንካራ ውይይቶችን እያደረግን ነው ብለዋል፡፡
ፕሮፌሰር መስፍን እንዳሉት የታጠቁ ኃይሎች እና ራሳቸውን ከምክክሩ ያገለሉ ፓርቲዎችን እንዲሳተፉ ለማድረግ ጥረቶች እየተደረጉ ነው።
“የታጠቁ ሀይሎችን እስካሁን ገጽ ለገጽ ወይም በቀጥታ አግኝተን አነጋግረናቸው አናውቅም፤ ነገር ግን መሳርያ አስነግቦ ወደ ጫካ ያስወረዳቸውን የፍትሀዊ ተጠቃሚነትንም ሆነ ሌላ የፖለቲካ ጥያቄ አቅርበው በምክክሩ እንዲሳተፉ በተለያየ መንገድ ጥሪ አድርገናል፤ ለድህንታቸው ሙሉ ዋስትና እንደምንሰጥ ከዛም አልፎ በውጭ ሀገራት ተገናኝተን ሀሳባቸውን እንዲያቀርቡ ሁኔታዎችን ለማመቻቸት ፈቃደኛ መሆናችንን ገልጸናል” ብለዋል ፕሮፌሰሩ።
“ከግጭት እና ጦርነት ያተረፍነው ሞት ሰቆቃ ውድመት እና የዕምሮ ስብራት ነው” ሲሉ የሚገልጹት ፕሮፌሰር መስፍን “እኛ የማደራደር ሀላፊነት ባይኖረንም እንኳን ለልዩነት እና ከዛም አልፎ ለግጭት ምክንያት የሆኑ ጉዳዮች ግን በጠረጴዛ ላይ ሰፍረው መፍትሄ የማያገኙ ከሆነ መጨረሻቸው በጎ እንደማይሆን እናምናለን” ይላሉ፡፡
የፖለቲካ ፓርቲዎችን ተሳትፎ በተመለከተ ኮሚሽኑ ስራ ሲጀምር አብረውት የሚሰሩ ፓርቲዎች ሁለት ብቻ የነበሩ ሲሆን በአሁኑ ወቅት 60 የሚጠጉ ፓርቲዎች ጋር አብሮ እንደሚሰራ እና አንዳንዶቹም በአማካሪነት እያገለገሉ ነው ተብሏል፡፡
ከዚህ ባለፈ አንዳንድ ፓርቲዎች ሁኔታዎች ሲቀያየሩ እና ከወቅታዊ የፖለቲካ ሁኔታ ጋር በተያያዘ የሽግግር መንግስት መቋቋም አለበት ፣ የሰላም እና ጸጥታ ሁኔታው መጽናት አለበት በሚሉ እና ተያያዥ ጉዳዮች በምክክሩ አንሳተፍም የሚሉ “የመውጣት እና መግባት” አዝማሚያ ያላቸው ፓርቲዎች እንዳሉ ዋና ኮሚሽነሩ ይገልጻሉ፡፡
አለመግባባቶች ወደ ግጭት እያደጉ በሚገኙበት በኦሮሚያ አንዳንድ አካባቢዎች እና በአማራ ክልል አሁንም ግጭቶች እየተካሄዱ በሚገኙበት ወቅት ካለመግባባት ወደ ግጭት ያደጉ ሁኔታዎችን በምክክር መፍታት ይቻላል የሚለው እምነትዎ አልተሸረሸረም ወይ? የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር መስፍን አርዓያን (ፕሮፌሰር) ጠይቀናል፡፡
“ምክክር ወደ እርቅ እና ሰላም የሚያደርስ መንገድ ነው በእርቅ ተስፋ ቆርጠሀል ማለት ከግጭት እና ጦርነት ጋር ለመኖር ወስንሀል ማለት ነው ፤ ነገር ግን ምክክር የሁለት አካላትን ይሁንታ የሚጠይቅ ነው ይህንን ስራ ስንጀምር 100 አመታት ድረስ ሄደን ለምንጋጭባቸው ችግሮች በሙሉ መፍትሄ እንሰጣለን ብለን አይደለም ነገር ግን ንትርክ እና ግጭትን የሚቀንስ በሂደትም ወደ መግባባት የሚወስዱ መንገዶችን መጥረግ ከቻልን ብለን ነው ስለዚህ እስካሁን ከሰራናቸው ስራዎችም አንጻር በቀላሉ ተስፋ የምቆርጥ አይደለሁም” ሲሉ መልሰዋል።
በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በየካቲት አጋማሽ 2014 ዓ.ም 11 ኮሚሽነሮችን ቃለ መሀላ አስፈጽሞ ወደ ስራ የገባው የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የሦስት ዓመት የቆይታ ዘመን እንዲኖረውም ተደርጓል።
ነገር ግን እንዳስፈላጊነቱ በተወካዮች ምክር ቤት የሥራ ጊዜው ሊራዘም እንደሚችል እና እድሜው መሰላት የሚጀምረው ኮሚሽነሮቹ ከተሾሙበት ዕለት ጀምሮ መሆኑም በኮሚሽኑ ማቋቋሚያ አዋጁ ላይ ተካቷል።
ከሚሽኑ የስራ ጊዜው ሊጠናቀቅ ከአምስት ወራት ያነሱ ጊዜያት በቀሩበት ሁኔታ በትግራይ እና አማራ ክልል ያልጀመራቸውን ስራዎች ጨምሮ ሀላፊነቱን ሙሉ ለሙሉ ማጠናቀቅ ይችላል ወይ? የሚለው በተደጋጋሚ የሚነሳ ጥያቄ ነው፡፡
ዋና ኮሚሽነሩ ለአመታት ሲንከባለሉ የመጡ ነገር ግን ለሰላም መደፍረስ እና ግጭት መንስኤ የሆኑ ችግሮችን መለየት እና ወደ መግባባት መድረስ እንደ ኢትዮጵያ ባለ የፖለቲካ እና የሰላም ሁኔታ ውስጥ አስቸጋሪ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡
አልአይን አማረኛ የኮሚሽኑ ጊዜ የሚራዘም ከሆነ እርሶ በሃላፊነት ይቀጥላሉ ወየ? ሲል ፕሮፌሰር መስፍንን ጠይቋል፡፡
“አሁን ባለው ሁኔታ የኮሚሽኑ ጊዜ እንዲራዘም አልፈልግም እንዲራዘምም አልጠየቅንም። በእርግጥ የትግራይ እና አማራ ክልሎች ላይ ያሉ ሁኔታዎች ባይዙን ኑሮ ከዚህ ቀደም ብለንም የምንጨርስበት ሁኔታ ነበር፤ ነገር ግን ከሎጂስቲክ ከትራንስፖርት እና ከሰላም ጋር የተያያዙ ሁኔታዎች ስራችንን በተገቢው ፍጥነት እንዳናከናውን እንቅፋት ሆነውብናል፤ አሁን እየሰራን ያለነው በቀረን ጊዜ ስራዎችን ለማጠናቀቅ ነው እድሜውን የማራዘም የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሀላፊነት ነው እኔ በግሌ ብጠይቀኝ ግን የኮሚሽኑ እድሜ እንዲራዘም ፍላጎት የለኝም” ብለዋል፡፡