ሄዝቦላ 70 የእስራኤል ወታደሮችን ገደልኩ አለ
እስራኤል በሊባኖስ ላይ ወረራ ከፈጸመች ጀምሮ 20 ወታደሮቿ እና ሄዝቦላ በሰሜን እስራኤል በፈጸመው ጥቃት ደግሞ 30 ወታደሮቿ መገደላቸውን ገልጻለች
ሄዝቦላ አሁን ላይ ከፍተኛ አመራሮቹ በእስራኤል የአየር ጥቃት በመገደላቸው ችግር ውስጥ ገብቷል
ሄዝቦላ 70 የእስራኤል ወታደሮችን ገደልኩ አለ።
የሄዝቦላ የዘመቻ ክፍል በዛሬው እለት እንደገለጸው ተዋጊዎቹ ከእስራኤል ኃይሎች ጋር ባደረጉት ውጊያ ከ70 በላይ የሚሆኑ የእስራኤል ወታደሮችን ገድለዋል ብሏል።
ሄዝቦላ ባለፈው ሳምንት ባወጣው መግለጫ የተገደሉ የእስራኤል ወታደሮች ቁጥርን 55 መሆናቸውን ገልጾ ነበር።
ሄዝቦላ ወታደሮቹ የተገደሉበት ጊዜ ከመቼ እስከ መቼ እንደሆነ የጊዜ ማዕቀፉን ግልጽ አላደረገም።
እስራኤል በሊባኖስ ላይ ወረራ ከፈጸመች ጀምሮ 20 ወታደሮቿ እና ሄዝቦላ በሰሜን እስራኤል በፈጸመው ጥቃት ደግሞ 30 ወታደሮቿ መገደላቸውን ገልጻለች።
እስራኤል ሟቹን የሄዝቦላ መሪ ይተካል ተብሎ ሲጠበቅ የነበረውን ሀሽም ሰይፈዲንን ከሶሰት ሳምንት በፊት በቤይሩት ከተማ ደቡባዊ ዳርቻ በፈጸመች ጥቃት መግደሏን በትናንትናው እለት አረጋግጣለች። ሄዝቦላም ዘግየት ብሎ ባወጣው መግለጫ የሰይፈዲንን መገደል አረጋግጧል።
"ነሰረላህን፣ ተተኪውን እና የሄዝቦላን ከፍተኛ አመራር አስወግደናል። ለእስራኤል ዜጎች ደህንነት ስጋት የሆነ ማንኛውም ሰው አያመልጠንም" ሲሉ የእስራኤል ጦር አዛዥ ሌፍትናንት ጀነራል ኸርዚ ሀለቬ ተናግረዋል።
እስራኤል በድንበር አካባቢ በመካከለኛው ምስራቅ የኢራን ጠንካራ አጋር ከሆነው ከሄዝቦላ ጋር ለአንድ አመት ያህል የተኩስ ልውውጥ ካደረገች በኋላ በሊባኖስ ላይ የእግረኛ እና የአየር ጥቃት ከፍታለች። ሄዝቦላ ወደ እስራኤል መተኮስ የጀመረው፣ በጋዛ ከእስራኤል ጋር እየተዋጋ ላለው ሀማስ አጋርነት ለማሳየት ሲሆን ሄዝቦላ አሁን ላይ ከፍተኛ አመራሮቹ በመገደላቸው ችግር ውስጥ ገብቷል።
እስራኤል በርካታ የሀማስ መሪዎችን እና መሰከረም 27 በፈጸመችው የአየር ጥቃት ተጽዕኖ ፈጣሪውን የሄዝቦላ መሪ ነስረላህን ከገደለች በኋላም ቢሆን በጋዛ እና በሊባኖስ የምታደርገውን ዘመቻ የመቀነስ ፍላጎት አላሳየችም።
ዲፕሎማቶች እስራኤል ከህዳሩ የአሜሪካ ምርጫ በፊት ወሳኝ ቦታዎች የመያዝ አላማ እንዳላት ተናግረዋል።
የእስራኤል-ሄዝቦላ ጦርነት ኢራን እና የእስራኤል አጋር የሆነችውን አሜሪካን ወደ ጦርነቱ ጎትቶ ያስገባል የሚል ስጋት ፈጥሯል።
ኢራን በእስራኤል ላይ የሚሳይል ናዳ ያዘነበችው የእስራኤልን የሊባኖስ ወረራ እና የሄዝቦላ መሪ ሀሰን ነስረላህግ ግድያ ለመበቀል ነበር።
ጥቃቱን ተከትሎ የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ኔታንያሁ "ኢራን ከባድ ስህተት ሰርታለች፤ ዋጋ ትከፍላለች" እና የእስራኤል ረጅም እጅ ኢራን ውስጥ የማይደርስበት ቦታ የለም" የሚሉ ዛቻዎችን ማሰማታቸው ይታወሳል።
ቀኑ አይታወቅ እንጂ እስራኤል በኢራን ላይ ጥቃት ለመክፈት ዝግጅቷን መጨረሷን የእስራኤል ባለስልጣናት ተናግረዋል። ኢራን በበኩሏ እስራኤል ጥቃት የምትሰነዝርባት ከሆነ የአጸፋ ምላሿ የከፋ እንደሚሆን ዝታለች።