የእንግሊዙ ዌስትሚኒስትር አቤይ ቅዱስ ታቦቱን ወደ ኢትዮጵያ ሊመልስ መሆኑን ገለጸ
ከኢትዮጵያ የተዘረው ታቦት በፈረንጆቹ በ1868 በተካሄደው የመቅደላ ጦርነት ከተዘረፉት በርካታ ቅርሶች አንዱ ነው
ዌስትሚኒስትር አቤይ ታቦቱን ወደ ኢትዮጵያ ለመመለስ "በመርህ ደረጃ መወሰኑን" ቃል አቀባይዋ ባለፈው ረቡዕ ተናግረዋል
የእንግሊዙ ዌስትሚኒስትር አቤይ ቅዱስ ታቦቱን ወደ ኢትዮጵያ ሊመልስ መሆኑን ገለጸ።
በእንግሊዝ ውስጥ በጣም ጠቃሚ ከሚባሉት ቸርቾች ወይም ቤተክርስቲያናት ውስጥ አንዱ የሆነው ዌስትሚኒስትር አቤይ ታቦቱን ወደ ኢትዮጵያ ለመመለስ "በመርህ ደረጃ መወሰኑን" ቃል አቀባይዋ ባለፈው ረቡዕ ተናግረዋል።
ታቦቱን ለመመለስ ውሳኔ ላይ የተደረሰው፣ በአለም ዙሪያ ያሉ ሙዚየሞች በቅኝ ግዛት ዘመን የተዘረፉ ቅርሶችን ለመመለስ በሚያስፈልጉ እርምጃዎች ላይ እየተወያዩ ባለበት ወቅት ነው።
ከኢትዮጵያ የተዘረው ታቦት በፈረንጆቹ በ1868 በተካሄደው የመቅደላ ጦርነት ከተዘረፉት በርካታ ቅርሶች አንዱ ነው።
በአሁኑ ወቅት በዌስትሚኒስትር አቤይ ውስጥ በልዩ ቦታ የተቀመጠው ታቦቱ በመጽሃፍ ቅዱስ ላይ ያሉት አስርቱ ትዕዛዛት የተጻፉበት እንደሆነ ይታመናል።
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ዘንድ ታቦት ቅዱስ የሆነ እና ቄሶች ብቻ ሊሸከሙት የሚችሉት ነው።
የዌስትሚኒስቴር አቤይ አስተዳደር ታቦቱን ለቤተክርስቲያኗ ለመመለስ በመርህ ደረጃ መስማማቱን ቃል አቀባይ ገልጸዋል።
"ይህን ለማስፈጸም ምርጥ የሚባሉ መንገዶችን እየፈለግን ነው፣ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ተወካዮችን ጋር ውይይት እያካሄድን ነው" ያሉት ቃል አቀባይዋ ጉዳዩ ውስብስብ እና ጊዜ የሚፈጅ ሲሉም አክለዋል።
በፈረንጆቹ 2021 ከእንግሊዝ፣ ከቤልጄም እና ከኔዘርላንድስ የንጉስ ጋሻ፣ በብር የተለበጠ ከቀንድ የተሰራ የተሰራ መጠጫ፣ በእጅ የተጻፈ መጽሀፍ እና መስቀልን ጨምሮ በርካታ ቅርሶች ወደ ኢትዮጵያ ተመልሰዋል።
አብዛኞቹ ቅርሶች እንግሊዞች ከንጉስ ቴዎድሮስ ዳግማዊ ጋር ያደረጉትን ጦርነት ተከትሎ ዘርፈው የወሰዷቸው ናቸው።