ፍልስጤማውያን ለወትሮው በደስታ ይቀበሉት የነበረውን ቅዱሱን የረመዳን ፆም በዝምታ ተውጠው ለመቀበል እየተዘጋጁ ናቸው
ፍልስጤማውያን በጥብቅ የእስራኤል ጸጥታ ቁጥጥር ውስጥ ሆነው ለወትሮው በደስታ ይቀበሉት የነበረውን ቅዱሱን የረመዳን ፆም በዝምታ ተውጠው ለመቀበል እየተዘጋጁ ናቸው።
በእስልምና እምነት ውስጥ ቅዱስ ከሚባሉት ስፍራዎች አንዱ በሆነው እና በአስር ሽዎች የሚቀጠሩ አማኞች የሚሰበሰቡበት አል አቅሳ መስጊድ በሚገኝበት በጥንታዊቷ እየሩሳሌም ከተማ በቪዎች የሚቆጠሩ የእስራኤል ፖሊሶች ተመድበዋል።
ይህ ቦታ በአይሁዳውያንም ቅዱስ ተደርጎ የሚወሰደው 'ቴምፕል ተራራ' መገኛ ሲሆን ጋዛን የተቆጣጠረው ሀማስ እና እስራኤል ጸብ መነሻ ምክንያት ሆኖም ቆይቷል።
በዚህ ቦታ በተነሳ ግጭት ምክንያት እስራኤል እና ሀማስ በ2021 ለ10 ቀናት ተዋግተዋል።
ይህ የ10 ቀናት ጦርነት ባለፈው ጥቅምት ወር በተቀሰቀሰው እና ስድስት ወራትን ካስቆጠረው ጦርነት አንጻር ሲታይ ትልቅ ተደርጎ የሚወሰድ አይደለም።
ሀማስ የእስራኤልን ድንበር ጥሶ ከባድ የተባለ ጥቃት በማድረስ በርካቶችን አግቶ ከ1200 በላይ ሰዎችን መግደሉን ተከትሎ በሁለቱ በመካከል እጅግ ከባድ የሚባል ጦርነት ተቀስቅሷል።
እስራኤል በጋዛ እየወሰደች ባለው መጠነሰፊ የአየር ድብደባ እና የእግረኛ ጦር ጥቃት እስካሁን የተገደሉ ፍልስጤማውያን ቁጥር 31ሺ አልፏል።
የቀኝ ዘመሙ የጸጥታ ሚኒስትር ባለፈው ወር በአል አቅሳ በሚገኙ አማኞች ላይ ገደብ እንደሚጣል መግለጻቸው መደናገር ፈጥሮ የነበረ ቢሆንም ጠቅላይ ሚኒስትር ኔታኔያሁ ግን ወደ መስጊዱ እንዲገቡ የተፈቀደው የአማኞች ቁጥር ከባለፈው አመት ጋር ተመሳሳይ ነው ሲሉ ተናግረዋል።
ረመዳን ሰኞ ወይም ማክሰኞ እንደሚጀመር ይጠበቃል። ነገርግን ከዚህ በፊት በጥንታዊቷ ከተማ ዙሪያ የሚደረጉ የማስዋብ ስራዎች እንደማይኖሩ እና እንደባለፈው አመት በዝምታ ድባብ እንደሚከበር ተገልጿል።
"የአዛውንቶች እና የልጆች ደም እንዲፈስ ስለማንፈልግ በዚህ አመት ጥንታዊቷ አየሩሳሌም አታጌጥም" ሲሉ በጥንታዊቷ እየሩሳሌም ኮሙኒቲ መሪ አማር ሲደር ተናግረዋል።
የእስራኤል ፖሊስ በበኩሉ ረመዳን በሰላም እንዲከበር ለማድረግ እና ጸብ አጫሪ ተግባራትን ለመቆጣጠር እንደሚሰራ ገልጿል።