ኢድ አል-ፊጥር መቼ ነው፤ በዓለም ዙሪያ እንዴትስ ይከበራል?
የረመዳን ፆም ሊጠናቀቅ መቃረቡን ተከትሎ በአለም ዙሪያ የሚገኙ ሙስሊሞች ለኢድ አልፈጥር በዓል ዝግጅት እያደረጉ ነው
የኢድ አል ፈጥር በዓል እንደ ሀገራቱ ከ1 ቀን እስከ 3 ቀናት በሚቆይ ፌስቲቫሎች ይከበራል
የታላቁ የረመዳን ጾም ወር ወደ መገባደጃው መቃረቡን ተከትሎ በመላው ዓለም ላይ የሚገኙ የእስልምና እምነት ተከታዮች የኢድ አል ፈጥር በዓልን ለማክበር በዝግጅት ላይ ይገኛሉ።
የዘንድሮ የኢድ አልፈጥር በዓል ነገ ማክሰኞ ወይም ረቡዕ እንደሚከበር ይጠበቃል።
የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ከሰሞኑ በሰጠው መግለጫ፥ የዒድ አል ፈጥር በዓል ጨረቃ ዛሬ ማታ ከታየች ነገ ማክሰኞ ሚያዚያ 1 ፥ ካልታየች ደግሞ ረቡዕ ሚያዚያ 2 ቀን አንደሚከበር አስታውቋል።
የስነ ከዋክብት ጥናት እንደሚያሳየው የረመዳን ወር በዚህ አመት 30 ቀናት እንደሚቆይ የሚጠበቅ ሲሆን፤ ይህም በሳዑዲ አረቢያ እና በብዙ አጎራባች ሀገራት የኢድ የመጀመሪያ ቀን ረቡዕ የመሆን እድሉ ሰፊ ነው።
የኢድ አልፈጥር የመጀመሪያ ቀን የሚወሰነው በእስልምና (ሂጅሪ) አቆጣጠር 10ኛው ወር የሸዋል ወር መጀመሩን የሚያመላክት ጨረቃ መታየቷን ተከትሎ ነው።
በዛሬው እለት የረመዳን ወር 29ኛው ቀን ጀንበር ከጠለቀች በኋላ፣ የሳዑዲ አረቢያ ኮሚቴ የጨረቃ ምልከታ የሚያደርግ ሲሆን፤ በዚህም ምሽት ላይ አዲስ ጨረቃ ከታየች ነገ ኢድ ይሆናል፤ ካልሆነ ሙስሊሞች የ30 ቀናትን ወር ለመጨረስ አንድ ተጨማሪ ቀን ይጾማሉ።
የዒድ አል ፈጥር በዓል እንዴት ይከበራል?
የኢድ አል ፈጥር በዓል የእስልምና እምነተ ተከታይ በሚበዙባቸው ሀገራት በተለምዶ ለሶስተ ቀና የሚከበር ሲሆን፤ እንደየ ሀገራቱ የበዓላቱ ቀናት ቁጥር ሊለያይ ይችላል።
ህዝበ ሙስሊሙ የኢድ ቀን አከባበርን የሚጀመረው ጎህ ሲቀድ በሚደረገው የጋራ የሰላት ስነስርዓት ላይ በመሳተፍ ነው።
ህዝበ ሙስሊሙ የጋራ ሰላት ወደ ሚደረግበት ስፍራ በጋራ ሲሄዱም “አላሁ አክበር” በማለት ተክቢራትን እያሰሙ ለፈጣሪ ምስጋና እያቀረቡ ነው።
ይህ ልዩ በዓል “ጣፋጭ” ኢድ በመባል በብዛት የሚታወቅ ሲሆን፤ በተለይም በመካከለኛው ምስራቅ ከኢድ ከሶላት በፊት ጣፋጭ መብላት የተለመደ ነው።
በተለይም በእነዚህ አካባቢዎች ከቴምር እና ሌሎች ጣፋጭ ነገሮች የተሰሩ ማሙል በመባል የሚታወቁ ብስኩቶችን መመገብ የተለመደ ተግር ነው።
በአብዛኞቹ ሀገራት አብዛኛውን ጊዜ ሙስሊሞች የኢድ ቀንን ጣፋጭ ነገሮችን በመያዝ ከቤት ቤት እየተዘዋወሩ ዘመዶቻቸውን እና ጎረቤቶቻቸውን በመጠየቅ ያሳልፋሉ።
ህጻናት ልጆችም አዲስ ልብስ ለብሰው ስጦታ እየተቀበሉ በዓሉን ተደስተው ያሳልፋሉ።
በኢድ አል ፈጥር እለት ሰዎች የበዓል መልካ ምኞች መግለጫዎቻቸውን በለያየ መልኩ የሚገልጹ ሲሆን፤ በብዛት በጥቅም ላይ ከሚውሉት የመልካም ምኞች መግለጫዎች ውስጥ ግን "ኢድ ሙባረክ" (የተባረከ ኢድ) ወይም "ኢድ ሰኢድ" (መልካም ኢድ) የሚሉት ተወዳጅና በስፋት ጥምቅ ላይ የሚውሉ ናቸው።