ፕሬዝዳንት ባይደን ወደ መሪነት በመጡ በሰዓታት ውስጥ 9 የትራምፕ ውሳኔዎችን ሻሩ
የአሜሪካና ሜክሲኮ ድንበር አጥር እንዲቆም እና አሜሪካ ወደ አየር ንብረት ለውጥ ስምምነት እንድትመለስም ተወስኗል
ፕሬዝዳንቱ ከቀለበሷቸው ፖሊሲዎች መካከል በ7 ሙስሊም የሚበዛባቸው ሀገራት ላይ የተጣለው የጉዞ እገዳ ይገኛል
በትናንትናው ዕለት 46ኛው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት በመሆን ቃለ መሀላ የፈፀሙት ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን በዓለ ሲመታቸው በተፈፀመ በጥቂት ሰዓታት ውስጥ 17 ፖሊሲዎች ተግባር ላይ እንዲውሉ ፊርማቸውን አኑረዋል፡፡
ፕሬዝዳንቱ ፊርማቸውን ካኖሩባቸው ፖሊሲዎች መካከል ዘጠኙ የቀድሞው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ውሳኔዎች የተሸሩባቸው ናቸው፡፡ በዚህም የተሰናባች ፕሬዝዳንትን ፖሊሲዎች እና ውሳኔዎችን በመቀልበስ አሜሪካ የ ጆ ባይደን ያክል ፈጣን እርምጃ የወሰደ መሪ ከዚህ ቀደም እንዳልነበራት ሲኤንኤን ዘግቧል፡፡
“ስራዬን ለመጀመር ከዛሬ የተሸለ ቀን የለም” ያሉት ፕሬዝዳንቱ “ለአሜሪካ ህዝብ የገባሁትን ቃል በመጠበቅ እጀምራለሁ” ሲሉ ፊርማቸውን ባኖሩበት ወቅት ለሪፖርተሮች ተናግረዋል፡፡
ባይደን ከሻሯቸው የትራምፕ ፖሊሲዎች መካከል የኮሮና ቫይረስ ፣ የድንበር ግንብ ፣ ሙስሊም ከሚበዛባቸው 7 ሀገራት የሚደረግ የጉዞ እገዳን የሚቀለብሱ እና የአየር ንብረት ጉዳይ ይገኙበታል፡፡
ፕሬዝዳንቱ ፊርማቸውን የጀመሩት ፣ ከ 400 ሺ በላይ አሜሪካውያንን ህይወት የቀጠፈውን የኮሮና ቫይረስ ለመከላከል ማስክ ማድረግን በሚያስገድደው ፖሊሲያቸው ነው፡፡ ከኮሮና ቫይረስ ጋር በተያያዘ ዝቅተኛ ትኩረት ከፍተኛ ትችትን ያስተናገዱት የቀድሞው ፕሬዝዳንት ትራምፕ ፣ ቫይረሱን በተደጋጋሚ ሲያጣጥሉተ መደመጣቸው ይታወቃል፡፡ አዲሱ ፕሬዝዳንት ሁሉም አሜሪካውያን ለ 100 ቀናት ማስክ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል፡፡ በፌዴራል መስሪያ ቤቶች ሁሉ ማስክ ማድረግ ግዴታ ሲሆን ሁሉም ግዛቶች እና የታችኛው እርከን አስተዳደሮች ተመሳሳይ እርምጃ እንዲወስዱም ታዘዋል፡፡
አሜሪካ በዓለም ጤና ድርጅት እንድትቀጥልም ባይደን የወሰኑ ሲሆን ዶ/ር አንቶኒዮ ፋውቺ በድርጅቱ የአሜሪካ ልዑክ መሪ እንዲሆኑ ሰይመዋቸዋል፡፡
የአየር ንብረት ለውጥን በተመለከተ ፣ አሜሪካን ወደ ፓሪሱ የአየር ንብረት ስምምነት እንድትመለስ ፕሬዝዳንት ባይደን ወስነዋል፡፡
ሙስሊም በሚበዛባቸው 7 ሀገራት ላይ ትራምፕ የጣሉትን የጉዞ እገዳ የቀለበሱት ባይደን ፣ በአሜሪካ እና ሜክሲኮ ድንበር ላይ የሚታጠረው አጥር ጉዳይ እንዲቆም አዘዋል፡፡
በዛሬው የመጀመሪያ ሙሉ የስልጣን ቀናቸው በኮሮና ቫይረስ ላይ ትኩረት ያደረጉ ተግባራትን ሲያከናውኑ እንደሚውሉ የሚጠበቁት ፕሬዝዳንት ባይደን በነገው ዕለት ደግሞ ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ በማተኮር ውሳኔዎችን ያስተላልፋሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡