ጆ ባይደን በሹመት ቀናቸው የትራምፕን ፖሊሲዎች ለመሻር መዘጋጀታቸው ተገለጸ
በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ፈቃድ የሌላቸው ሰዎች ዜግነት የሚያገኙበት ዕድልም ይፈጠራል ተብሏል
ሙስሊም በሚበዛባቸው 7 ሀገሮች ላይ የተጣለውን የጉዞ እገዳ ማንሳት በሹመታቸው ቀን ከሚወስኗቸው ጉዳዮች አንዱ ነው
ተመራጩ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን በመጀመሪያው የስልጣን ቀናቸው አነጋጋሪ የነበሩትን የትራምፕ ፖሊሲዎች ሊያስወግዱ መዘጋጀታቸውን የኋይት ሀውስ ሰራተኞች ኃላፊ ለመሆን በባይደን የተመረጡት ሮን ክሌይን አስታውቀዋል፡፡
የፓሪሱን የአየር ንብረት ስምምነት እንደገና መቀላቀል እና ሙስሊም በሚበዛባቸው ሀገሮች ላይ የተጣለውን የጉዞ እገዳ ማንሳት በቅጽበት ከሚቀየሩ የትራምፕ ፖሊሲዎች መካከል መሆናቸውን የአሜሪካ ሚዲያዎች ዘግበዋል፡፡
በትራምፕ ፖሊሲ በሜክሲኮ ድንበር እየተያዙ ከወላጆቻቸው የተለዩ ህጻናትን ዳግም ከወላጆቻቸው ጋር እንዲገናኙ ማድረግም ፣ ባይደን በፍጥነት የሚተገብሩት ተለዋጭ ፖሊሲ እንደሚሆን ተገልጿል፡፡ ከኮሮናቫይረስ ጋር በተያያዘ ፣ ማስክ ማድረግን ጨምሮ ሌሎች አስገዳጅ ህጎችን ሊያጸድቁ እንደሚችሉም የኋይት ሀውስ ኃላፊው መረጃ ያመለክታል፡፡
በመጀመሪያ የስልጣን ቀናቸው ከሚያሳልፏቸው ውሳኔዎች በተጨማሪ ፣ በ100 ቀናት የስልጣን ጊዜያቸው ፣ በርካታ ስደተኞችን ተጠቃሚ የሚያደርግ አዲስ የስደተኞች ህግ ለኮንግረሱ እንደሚያቀርቡ ይጠበቃል፡፡ በዚህም አሁን ላይ በአሜሪካ የሚገኙ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ህጋዊ የመኖሪያ ፈቀድ የሌላቸው ስደተኞች የሀገሪቱን ዜግነት የሚያገኙበት መንገድ እንደሚከፈትላቸው ነው የሲኤንኤን ዘገባ የሚያሳየው፡፡
ከሦስት ቀናት በኋላ 46ኛው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ሆነው የሚሾሙት ጆ ባይደን በኮሮናቫይረስ ምክንያት የተጎዳውን የአሜሪካ ኢኮኖሚ ለማነቃቃት የ 1.9 ትሪሊዮን ዶላር የድጎማ ገንዘብ ይፋ በማድረግ ወረርሽኙን መከላከል ቅድሚያ የሚሰጡት ጉዳይ መሆኑን አሳይተዋል፡፡
በአሜሪካ እስካሁን ከ24 ሚሊዮን በላይ ሰዎች በኮሮና ተይዘው ከ400 ሺ በላይ ሰዎች ህይወታቸውን አጥተዋል፡፡ ቫይረሱ የትራምፕ አስተዳደር ከፍተኛ ፈተና እንደሚሆን ይጠበቃል፡፡ በሀገሪቱ ያለው የፖለቲካ ቀውስም ሌላው ከባድ ፈተና ነው፡፡
የትራምፕ ደጋፊዎች በጦር መሳሪያ የታጀበ ሰልፍ ያደርጋሉ በሚል ስጋት በአሁኑ ወቅት በሁሉም የአሜሪካ ግዛቶች የጸጥታ ኃይሎች በተጠንቀቅ ላይ ናቸው፡፡