ለጆ ባይደን በዓለ ሲመት የሚሰማሩ ሁሉም ወታደሮች ላይ ማጣራት እየተደረገ ነው
ከውስጥ ጥቃት እንዳይፈጸም በሚል ስጋት ነው በወታደሮቹ ላይ ማጣራት የሚደረገው
ከአሜሪካ የተለያዩ አካባቢዎች 25 ሺ የብሔራዊ ዘብ አባላት ወደ ዋሺንግተን እየገቡ ነው
ከነገ በስቲያ ረቡዕ ዕለት የሚካሔደው የተመራጩ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን በዓለ ሲመት በትራምፕ ደጋፊዎች እንዳይታወክ በመስጋት በርካታ የብሔራዊ ጥበቃ ወታደሮች ወደ ዋሺንግተን በመግባት ላይ ናቸው፡፡ ለዝግጅቱ ወደ ዋና ከተማዋ የሚገቡት የብሔራዊ ጥበቃ አባላት ታዲያ የተለያየ የማጣራት ስራ ይከናወንባቸዋል፡፡
ከውስጥ ጥቃት ሊፈጸም ይችላል በሚል ስጋት ነው ኤፍቢአይ 25 ሺ የብሐየራዊ ጥበቃ ወታደሮች ላይ የማጣራ ስራ በማከናወን ላይ የሚገኘው፡
ይህ አንድ በአንድ የማጣራት ድርጊት ፣ የተሰናባቹ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ደጋፊዎች ታህሣሥ 28 ቀን 2013 ዓ.ም የፈጸሙትን የአመፅ ድርጊት ተከትሎ የተፈጠረውን ልዩ የደህንነት ስጋት የሚያንፀባርቅ ነው ተብሏል፡፡
የአሜሪካ ጦር ኃይሎች ፀሐፊ ሪያን ማካርቲ ባለሥልጣናት አደጋውን እንደሚገነዘቡ ገልፀው ፣ በዓለ ሲመቱ በመቃረቡ የጦሩ አዛዦች በየደረጃቸው ያሉ ማናቸውንም ችግሮች በትኩረት እንዲከታተሉ አስጠንቅቀዋል፡፡ ፀሐፊው “እስካሁን ድረስ ግን ምንም ዓይነት ለስጋት የሚዳርግ ማስረጃ አላየንም” ያሉ ሲሆን “የማጣራት ስራውም የሚከናወነው ለጥንቃቄ እንጂ የሚታወቅ ስጋት ስላለ አይደለም” ብለዋል፡፡
እሁድ እለት ከ አሶሺየትድ ፕሬስ ጋር ቃለ ምልልስ ያደረጉት ሚስተር ማካርቲ "ያለማቋረጥ በሂደቱ ውስጥ እያለፍን ሲሆን ለሁለተኛ፣ ለሦስተኛ ጊዜ ደጋግመን ለዚህ ተግባር የተመደቡትን እያንዳንዱን ግለሰብ እንመለከታለን" ብለዋል፡፡ የጥበቃ አባላትም ሊፈጠሩ የሚችሉ የውስጥ አደጋዎችን ለይቶ ለማወቅ የሚያስችል ሥልጠና እያገኙ ነው ብለዋል፡፡
ለበዓለ ሲመቱ 25,000 የብሔራዊ ጥበቃ አባላት ከመላ ሀገሪቱ ወደ ዋሽንግተን እየገቡ ናቸው፡፡ ይህም ከዚህ ቀደም ለፕሬዝዳንታዊ በዓለ ሲመት ከሚመደቡት ቢያንስ በሁለት ተኩል እጥፍ ይበልጣል፡፡
ከዚህ ቀደም በእንደዚህ አይነት ዝግጅቶች ላይ የሀገር ውስጥ ጥቃቶች አልቃኢዳን እና አይኤስን ከመሰሉ የጽንፈኛ ቡድኖች ሊፈጸሙብኝ ይችላሉ በሚል ጥንቃቄ የምታደርገው አሜሪካ ፣ አሁን የተገላቢጦሽ ሆኖ ስጋቷ ከራሷ በተወለዱ የትራምፕ ደጋፊዎች ፣ የነጭ የበላይነት አቀንቃኞች ፣ አክራሪ የቀኝ ዘመምተኞች እና መሰል አክራሪ ቡድኖች የሚመነጭ ሆኗል፡፡
ባለፈው ታህሣሥ 28 የትራምፕ ደጋፊዎች የሀገሪቱ መንግስት መቀመጫ የሆነውን ካፒቶል ሂልን ሰብረው በመግባት ለአምስት ሰዎች ሞት ምክንያት መሆናቸው ይታወሳል፡፡