በአዲስ አበባ ሁለት ሕፃናትን በአሰቃቂ ሁኔታ የገደለችው ግለሰብ የሞት ቅጣት ተፈረደባት
ተከሳሿ ድርጊቱን አልመፈጸሟን ብትክድም የሰው እና የሰነድ ማስረጃዎችን መከላከል አልቻለችም
አለመማሯን እና ለፖሊስ እጇን መስጠቷን በማቅለያነት ብታቀርብም ፍርድ ቤቱ ማቅለያዋን አልተቀበለውም
በአዲስ አበባ ሁለት ሕፃናትን በአሰቃቂ ሁኔታ የገደለችው ግለሰብ የሞት ቅጣት ተፈረደባት።
የቅጣት ውሳኔውን የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ ሰው ግድያና ከባድ ውንብድና ወንጀል ችሎት ነው ያሳለፈው።
ህይወት መኮንን የተባለችው ተከሳሽ ነሃሴ 26 ቀን 2014 ዓ/ም በለሚኩራ ክፍለ ከተማ አራብሳ ኮንዶሚኒዬም በቤት ሰራተኛነት ተቀጥራ በምትሰራበት ወቅት ሁለት ህጻናትን በአሰቃቂ ሁኔታ ገድላለች በሚል ነው የተከሰሰችው።
ከከባድ የግድያ ወንጀሉ ባሻጋር ተከሳሽ የሟቾችን የቤተሰብ ሰነድ ማስረጃዎች በማጥፋትም ጥቅምት 15 ቀን 2015 ዓ.ም ተደራራቢ ክስ ተመስርቶባት እንደነበር የፍትህ ሚኒስቴር መረጃ ያስረዳል።
ተከሳሿ አስቀድማ ለፖሊስ ወንጀሉን መፈጸሟን ብታምንም በዐቃቤ ህግ ክስ ተመስርቶ ፍርድ በቤት ቀርባ ወንጀሉን ስለመፈጸሟ ስትጠየቅ “ድርጊቱን አልፈጸምኩም ጥፋተኛም አይደለሁም” የሚል ምላሽ ስጥታለች።
ይሁን እንጂ ዐቃቤ ህግ ያቀረበውን የሰው እና የሰነድ ማስረጃዎች መከላከል አልቻለችም፤ የመከላከያ ማስረጃ የለኝም በማለቷም ፍርድ ቤቱ የጥፋተኝነት ፍርድ ሰጥቷል፡፡
የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ ሰው ግድያና ከባድ ውንብድና ወንጀል ችሎት ዛሬ ባስቻለው ችሎት፥ ዐቃቤ ህግ በቅጣት አወሳሰን መመሪያ መሰረት ወንጀሉ ከባድ ደረጃ ተብሎ እንዲሰላለትና በሞት እንድትቀጣ አስተያየት ሰጥቷል፡፡
ተከሳሽ በበኩሏ ከዚህ ቀደም ወንጀል ፈፅማ አለማውቋን፣ ወንጀሉን የፈጸመችው ከእውቀት ማነስና ባለመማሯ መሆኑን ፤ እጇን ለፖሊስ መስጠቷን የቅጣት ማቅለያ አድርጋ አቅርባለች።
ይሁን እንጂ ፍርድ ቤቱ ማቅለያዋን አልተቀበለውም፡፡
ሌሎች አጥፊዎችን ያስጠነቅቃል በማለትም ተከሳሿ በሞት እንድትቀጣ ሲል ወስኖባታል፡፡