ኢትዮጵያዊው አትሌት በትውልደ ኬንያዊቷ አትሌት ግድያ ተጠረጠረ
ትውልደ ኬንያዊቷ አትሌት ሙቱዋ በስለት ተወግታ ህይወቷ ማለፉ የኬንያ ፖሊስ አስታውቋል
በግድያ የተጠረጠረው ኢትዮጵያዊው አትሌት እስክንድር ሀይለማርያም አሁን ላይ ከኬንያ እንደሸሸም ተገልጿል
ኢትዮጵያዊው አትሌት፤ በትውልደ ኬንያዊቷን አትሌት ዳማሪስ ሙዜ ሙቱዋ ግድያ ዋና ተጠርጣሪ እንደሆነ የኬንያ ፖሊስ አስታወቀ፡፡
የኬንያዋ ኢልጋዮ ማራክዌት ፖሊስ “ዋና ተጠርጣሪ የሆነውን የአትሌቷ እጮኛ ኢትዮጵያዊ አትሌት እየፈለግኩ” ነው ብለዋል፡፡
ፖሊስ ለአትሌቷ ግድያ ዋና ተጠርጣሪ አድርጎ እየፈለገ ያለው ፍቅረኛዋም፤ እስክንድር ሀይለማርያም ፎሊን የተባለ ኢትዮጵያዊ አትሌት መሆኑን ታውቋል፡፡
እስክንድር ሀይለማርያም አሁን ላይ ከኬንያ እንደሸሸም ፖሊስ ገልጿል።
የኢቴን ከተማ ፖሊስ አዛዥ ቶም ማኮሪ ፤ ከሙቱዋ ጋር የፍቅር ግንኙነት የነበረው ኢትዮጵያዊው አትሌት፤ ከኬንያ ከመሸሹ በፊት ሟቿ አትሌት ልምምድ በምታደርግበት ተቋም ውስጥ ሲሰለጥን ነበር ብለዋል።
የፖሊስ አዛዡ "ተጠርጣሪው(እስክንድር) አብሮ ልምምድ ወደሚያደርግ ጓደኛው ደውሎ የሴት ጓደኛውን መግደሉን እና አስክሬኗ ቤት ውስጥ እንዳለ ተናግሯል" ሲሉ ለሮይተርስ ተናግሯል።
አትሌት ዳማሪስ ሙዜ ሙቱአ ኢቴን ተብላ በምትጠራው ከተማ ሕይወቷ አልፎ ሲገኝ አስክሬኗ ፈራርሶ ነበርም ብለዋል።
ፖሊስ የ28 ዓመቷ አትሌት ሕይወቷ ያለፈው በስለት ከተወጋች በኋላ እንደሆነም ገልጿል፡፡
የኬንያ ፖሊስ መረጃ እንደሚያመለክተው ከሆነ፤የ28 ዓመቷ አትሌት ተገደለችው ባሳለፍነው ቅዳሜ ነው፡፡
የፖሊስ አዛዡ በወንጀሉ ተጠርጣሪ ነው የተባለው ኢትዮጵያዊ አትሌት ወደ የት ሀገር እንደሸሸ ያሉት ነገር የለም።
አትሌቷ የተገደለችባት ኢቴን ከተማ የበርካታ አትሌቶች መኖሪያ ስትሆን ከጥቂት ወራት በፊት በተመሳሳይ አግነስ ትሮፕ የተባለች አትሌት በከተማዋ በመገደሏ ድንጋጤን ፈጥሮ ነበር።
አትሌት አግነስ በቶኪዮ ኦሎምፒክ በ5ሺህ ሜትር 4ኛ ደረጃን ይዛ አጠናቃ ነበር።
የአግነስ ትሮፕ ባለቤት በአትሌቷ ግድያ በቁጥጥር ስር ውሎ እንደሚገኝም ይታወቃል።