በኮሮና ቫይረስ ስጋት ቻይና ዜጎቿን ከኢራን ልታስወጣ ነው
በኮሮና ቫይረስ ስጋት ቻይና ዜጎቿን ከኢራን ልታስወጣ ነው
የኮሮና ቫይረስ እስካሁን 75 ሀገራትን ማዳረሱ ተረጋግጧል፡፡ በነዚህ ሀገራት በድምሮ ከ90 ሺ በላይ ሰዎች በቫይረሱ የተያዙ ሲሆን ከ 3,100 በላይ ሰዎች ህይወታቸውን አጥተዋል፡፡
ቻይና፣ ደቡብ ኮሪያ፣ ጣሊያን እና ኢራን አብዛኛው ተጠቂዎች የሚገኙባቸው ሀገራት ናቸው፡፡
ከ10 ሺ በላይ የሚሆኑት ተጠቂዎች ከቻይና ውጭ ቫይረሱ በተዳረሰባቸው ሀገራት የሚገኙ ሲሆኑ ባጠቃላይ በቫይረሱ ምክንያት ከተመዘገበው ሞት ከ120 በላይ የሚሆኑት ከቻይና ውጭ ናቸው፡፡
ቻይና
በቻይና እስካሁን በቫይረሱ መያዛቸው የተረጋገጠ ሰዎች ቁጥር 80,302 ሲሆን 2,946 ሰዎች ሞተዋል፡፡ 47,270 ሰዎች ደግሞ አገግመው ከሆስፒታል ወጥተዋል ነው የተባለው፡፡
ሀገሪቱ በዛሬው እለት 125 አዳዲስ ተጠቂዎችን ብቻ ነው ሪፖርት ያደረገችው፡፡ ይሄም ከጥር ወር ወዲህ ዝቅተኛው ነው ተብሏል፡፡
የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ እያደገ ሲሄድ በኢራን የሚገኘው የቻይና ኤምባሲ ቻይናውያን ዜጎችን ከሀገሪቱ ለማስወጣት አቅዶ እየሰራ መሆኑን አስታወቀ፡፡
ቻይናውያንን ከኢራን የሚያስወጣው የመጀመሪያው የቻርተር በረራ ማክሰኞ ማታ ወደ ኢራን እንደሚደርስ ግሎባል ታይምስን ጠቅሶ ሲኤንኤን ዘግቧል፡፡
በኢራን ዋነኛ የቫይረሱ ተጠቂዎች መነሻ በሆነችው የሀገሪቱ ቅድስት ከተማ ቆም የሚገኙ ቻይናውያን ተማሪዎች ወደ ሀገራቸው ለመመለስ ከተመዘገቡት መካከል ይገኛሉ፡፡
በኢራን ከፍተኛ የመንግስት አማካሪን ጨምሮ 77 ሰዎች በቫይረሱ መሞታቸውን ቴህራን አስታውቃለች፡፡
አሜሪካ
በኮሮና ቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ከ100 በላይ የደረሰባት አሜሪካ በተያዘው ሳምንት ውስጥ ብቻ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ዜጎቿን እንደምትመረምር አስታውቃለች፡፡
የሀገሪቱ የጤናው ዘርፍ ባለስልጣናት የተጠቂዎች ቁጥር በፍጥነት ሊያሻቅብ እንደሚችል መግለጻቸውን ተከትሎ ነው በብዛት ምርመራ እንዲደረግ የተወሰነው፡፡
እስካሁን በ12 የአሜሪካ ግዛቶች ተጠቂዎች መኖራቸው የተረጋገጠ ሲሆን 6 ሰዎች የሞቱባቸው ካሊፎርኒያና ዋሺንግተን ዋነኛ ሰለባዎች ናቸው፡፡
በቫይረሱ ከተያዙት መካከል አንድ አራተኛው ወደሌሎች ሀገራት ያልተጓዙ እና እዚያው በሀገራቸው ከሌሎች ታማሚዎች የተላለፈባቸው መሆኑ ደግሞ ዋሺንግተንን ይበልጥ ያሳሰባት ጉዳይ ነው፡፡
እንግሊዝ
አንድ አምስተኛ የሚሆኑ እንግሊዛውያን ሰራተኞች ከኮሮና ቫይረስ እየተስፋፋ መምጣት ጋር ተያይዞ ስራ ሊያቆሙ እንደሚችሉ የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን ተናግረዋል፡፡
ቦሪስ ጆንሰን በሰሜን ለንደን ላቦራቶሪ ሲጎበኙ
እስከ ማክሰኞ የካቲት 24 ቀን 2012 ዓ.ም ድረስ በእንግሊዝ የቫይረሱ ተጠቂዎች ቁጥር 40 ደርሷል፡፡ የሀገሪቱ ጤና ዲፓርትመንት እንዳስታወቀው ምርመራ ከተደረገላቸው 14,525 ሰዎች መካከል ነው 40 ተጠቂዎች የተለዩት፡፡
የበሽታው አሳሳቢነት እየጨመረ ከመሆኑ ጋር በተያያዘ፣ ስርጭቱን ለመግታት የሚደረገውን ጥረት የሚያግዙ ወታደሮችም በተጠንቀቅ እንዲቆሙ መደረጉን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡
ፈረንሳይ
የቫይረሱ ስርጭት ያሳሰባት ፈረንሳይ ከ1,200 በላይ ትምህርት ቤቶችን ዘግታለች፡፡ ትምህርት ቤቶቹ የተዘጉት ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ተጠቂዎች ሪፖርት በተደረጉባቸው አካባቢዎች ነው፡፡
በፈረንሳይ እስካሁን 191 የቫይረሱ ተጠቂዎች መኖራቸው እና ሶስት ሞት መመዝገቡ ተዘግቧል፡፡
በሰሜን ፓሪስ የመጀመሪያ ደረጃ እና የሁለተኛ ደረጃ ት/ቤቶች የተዘጉ ሲሆን መቼ እንደሚከፍቱ የታወቀ ነገር የለም ፡፡
ኢራን
በኢራን የኮሮናቫይረስ ሟቾች ቁጥር 77 ደርሷል፡፡
እስካሁን በሀገሪቱ በድምሩ 2,336 የሚሆኑ የኮሮናቫይረስ ተጠቂዎች መኖራቸው ሲረጋገጥ ከነዚህም 23 የሚሆኑት የፓርላማ አባላት ናቸው፡፡
የሀገሪቱ ምክትል የጤና ሚኒስትሩ አሊሬዛ ራይሲ ለመገናኛ ብዙሃን ባደረጉት ገለጻ ባለፉት 24 ሰዓታት ውስጥ 835 አዳዲስ ተጠቂዎች መለየታቸውንና 11 ሰዎች መሞታቸውን ተናግረዋል ፡፡
በህክምና ላይ የሚገኝ ታማሚ በኢራን
ሕመሙ ከመነጨባት ከቻይና ቀጥሎ በኮሮናቫይረስ በሽታ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሰዎች የሞቱት በኢራን ነው፡፡
በእስላማዊ ሪታብሊኳ ሀገር ትክክለኛው የሟቾች ቁጥር ከተጠቀሰው ሊበልጥ እንደሚችል በብዙዎች ዘንድ ይታመናል ፡፡
ደቡብ ኮሪያ
በደቡብ ኮሪያ ከ5,100 በላይ ተጠቂዎች ሲገኙ 31 ሰዎች በቫይረሱ ሞተዋል፡፡
ጃፓን
ጃፓን እስከዛሬ ድረስ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር በሀገሪቱ 980 መድረሱን አረጋግጣለች፡፡
ጣሊያን
በጣሊያን የቫይረሱ ተጠቂዎች ቁጥር ከ1,600 በላይ ደርሰዋል፡፡ ሀገሪቱ 34 ሰዎችን ደግሞ በዚሁ በሽታ ተነጥቃለች፡፡ ሌሎች የአውሮፓ ሀገራትም በብዛት ለቫይረሱ የተጋለጡት ከጣሊያን ነው፡፡
ጀርመን 188፣ ኖርዌይ 28፣ ሰዊዲን 24 ተጠቂዎች መኖራቸውን ሪፖርት አድርገዋል፡፡
በአፍሪካ ሴኔጋል፣ግብጽ፣ናይጄሪያ፣ አልጄሪያ፣ ቱኒዚያ፣ ሞሮኮ ቫይረሱ የተዳረሰባቸው ሀገራት ናቸው፡፡
ለዘገባው የተለያዩ ምንጮችን በዋቢነት ተጠቅመናል፡፡