ዛምቢያ በነገው እለት ፕሬዘዳንታዊ ምርጫ ታካሂዳለች
ምርጫው ዲሞክራሲያዊ ስርዓትን በመዘርጋት ለምትታወቀው ዛምብያ ያላትን ምስል ለማስቀጠል የምትፈተንበት መሆኑንም ተዘግቧል
የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ኤድጋር ሉንጉ በድጋሚ ለመመረጥ በዕጩነት ቀርበዋል
ዛምቢያ በነገው እለት በምታካሂደው ምርጫ ፕሬዝዳንቱ ከአንጋፋው የተቃዋሚ ፓርቲ መሪ ሃካዪንዴ ሂቺሌማ ብርቱ ፉክክር እንደሚገጥማቸው ከወዲሁ ተጠብቀዋል፡፡
አንዳንድ ተንታኞች እንደሚሉት ከሆነም ምርጫው የፖለቲካ ቀውስ ሊቀሰቀስ ይችላል እያሉ ነው።የፕሬዝዳንት ሉንጉን ተቺዎች ፕሬዝዳንቱ ከወዲሁ “አንዳንድ የመገናኛ ብዙሃን አውታሮችን በመዝጋት፣ ተቃዋሚዎችን በማሰር እና የሚተቿቸውን ሰዎች በማሳደድ ዲሞክራሲያዊ መብቶችን እያፈኑ ነው” ይሏቸዋል።
ሂዩማን ራይትስ ባለፈው ሰኔ ባወጣው ሪፖርቱ ሉንጉ ዛምቢያን ወደሰብዓዊ መብት ቀውስ አፋፍ እየወሰዱዋት መሆናቸውን ነቅፎ ነበር፡፡ የሀገሪቱ ምርጫ ኮሚሽን ባለፈው ግንቦት ወር ማንኛውም ዓይነት የምርጫ ቅስቀሳ ዘመቻ እንዳይደረግ ቢያግድም ገዢው ፓርቲ እና ተቀዋሚዎች የፊት ማስክ ላመደል በሚል ሽፋን የምርጫ ቅስቀሳ ሲያደርጉ ተስተውለዋል፡፡
ኤድጋር ሉንጉ በመሰረተ ልማት ኢንቨስትምንታና በመዓድን ዙርያ ዘመቻ በማካሄድ ላይ ናቸው፡፡ ፕሬዝዳንቱ በሀገሪቱ ኢኮኖሚ የ70 በመቶ ድርሻ ያለውን ኮፐር ለፖለቲካ መሳርያ መጠቀማቸው ተገቢ አለመሆኑንም በርካቶች በማንሳት ላይ ናቸው፡፡
የሀገሪቱ ባለሀብቶች በኮፐር አምረቿ ሀገር በነገው እለት የሚካሄደውን ምርጫ በቅርበት እየተመለከቱት ይገኛል፡፡ የዓለም አቀፉ ገንዘብ ድርጅት/አይአምኤፍ/ በበኩሉ ለድሃ ሀገራት እንደሚያደርገው ድጋፍ ሁሉ ለዛምብያ የሚያደርገው ድጋፍ ምርጫው አስኪያልፍ ገታ ለማድረግ መስማማቱን አስታውቋል፡፡