ዛምቢያ በኮሮና ቫይረስ መስፋፋት ምክንያት የምሽት መዝናኛ ቦታዎችን ዘጋች
በዛምቢያ ባለፉት ቀናት በቀን ከአንድ ሺህ በላይ ዜጎች በቫይረሱ እየተጠቁ ነው
ዛምቢያ እገዳውን የጣለችው ለቀጣዮቹ 14 ቀናት ነው
ዛምቢያ በኮሮና ቫይረስ መስፋፋት ምክንያት የምሽት መዝናኛ ቦታዎችን ዘጋች።
አገሪቱ እንዳሳወቀችው የምሽት ክለቦች፣ የቁማር ቤቶች፣ የስፖርት ቤቶች እና ሌሎች መዝናኛ ስፍራዎች ለሁለት ሳምንት ተዘግተው እንዲቆዩ መወሰኑን ሲጂቲኤን አፍሪካ ዘግቧል።
እነዚህ መዝናኛ ስፍራዎች በሳምንት ሶስት ቀናት ብቻ ለተወሰኑ ሰዓታት እና የውጭ (ቴክአዌይ) አገልግሎት ብቻ እንዲሰጡ መወሰኑ ተገልጿል።
የሀይማኖት ስፍራዎች ግን በጥንቃቄ የሚጠበቁ የዓምልኮ ስነ ሰርዓቶችን ማካሄድ ይችላሉ ተብሏል።
የቫይረሱ ስርጭት በዚሁ ከቀጠለ በቀጣይ የብዙሃን ትራንስፖርት እና መገበያያ ስፍራዎች ሊዘጉ እንደሚችሉም የአገሪቱ መንግስት አሳስቧል።
ዛምቢያ በዚህ ዓመት ማካሄድ የነበረባትን እና የተራዘመውን ምርጫ ለማካሄድ የምረጡኝ ቅስቀሳ ዘመቻዎች በመካሄድ ላይ ቢሆኑም ትምህርት ቤቶች ግን እስካሁን ድረስ ተዘግተዋል።
ባለፉት 24 ሰዓታት 1 ሺህ 93 ሰዎች በኮሮና ቫይረስ ሲያዙ በአጠቃላይ 150 ሺህ ገደማ ዜጎች በቫይረሱ ተጠቅተዋል።
በአጠቃላይ 2 ሺህ 91 ሰዎች ደግሞ በዚህ ቫይረስ ምክንያት ህይወታቸውን ሲያጡ ዛምቢያ በሶስተኛው ዙር የኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት ክፉኛ እየተጠቁ ካሉ አገራት መካከል ዋነኛዋ ናት።
በዚህም ምክንያት ዛምቢያን ጨምሮ ሌሎች የደቡብ አፍሪካ አገራት በእንግሊዝ፤የተባበሩት አረብ ኢምሬት እና ሌሎች የአውሮፓ አገራት የጉዞ እቀባ ተጥሎባቸዋል።