ዩኤኢ ከዛምቢያ፣ ዲ.አር. ኮንጎ እና ኡጋንዳ የሚነሱ መንገደኞች ከአርብ ጀምሮ ወደ ሀገሯ እንዳይገቡ አገደች
የጉዞ ክልከላው የተጣለው የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ስርጭትን ለመከላከል ነው
በሦስቱ ሀገራት በኮቪድ 19 የሚያዙ ሰዎች ቁጥር በፍጥነት እየጨመረ ነው
የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች ከዛምቢያ፣ ከዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ እና ከኡጋንዳ የሚነሱ መንገደኞች ከፊታችን አርብ ጀምሮ ወደ ሀገሯ መግባት እንደማይችሉ አስታወቀች።
ከሦስቱ ሀገራት የሚነሱ ተጓዦች ወደ ተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች እንዳይገቡ ክልከላ የተጣለውም የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ስርጭትን ለመከላከል ታስቦ እንደሆነ የኤሚሬትስ ዜና ወኪልን ጠቅሶ ሲ.ጂ.ቲ.ኤን ዘግቧል።
ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ባሳለፍነው ሳምንት ላይ ሦስተኛ ዙር የኮሮና ቫይረስ ማእበል ወረርሽኝ መከሰቱን በመግለጽ፤ አሁን ያለው ሁኔታም አሳሳቢ መሆኑን አስታውቃለች።
ካለፉት 4 ወራት ወዲህ በቫይረሱ የሚያዙ እና ህይወታቸው የሚያልፍ ሰዎች ቁጥር በከፍተኛ መጠን ሊጨምር እንደሚችልም ሀገሪቱ ማስታወቋ አይዘነጋም።
የዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎዋ ኪንሻሳ ከተማ ከፍተኛ የወረርሽኙ መጠን የሚገኝባት ሲሆን፤ የከተማዋ ነዋሪዎች የኮቪድ 19 መከላከያዎቸን መተግበር ላይ ቸልተኛ መሆናቸውም ተነግሯል።
ኡጋንዳም የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ሁለተኛ ማእበል ያጋጠማት ሲሆን፤ አሁን ያለው ወረርሽኝ ከዚህ ቀደም ከተከሰተው የከፋ ነው ሲሉም ነው የጤና ባለሙያዎች የሚናገሩት።
ባለፉት 10 ቀናት ብቻ ኡጋንዳ ከ5 ሺህ በላይ ዜጎቿ በኮቪድ 19 ሲያዙባት 20 ዜጎቿን በቫይረሱ ሳቢያ አጥታለች፤ አብዛኞቹ ተጠቂዎችም ከዋና ከተማዋ ካምፓላ እንደሆኑ ነው ተሰማው።
ዛምቢያም በሦስተኛ ዙር የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ማእበል የተመታች ሲሆን፤ የሀገሪቱ መንግስት አሁን ባለው ሁኔታ የተጠቂዎች መጠን መጨመር የሀገሪቱን የጤና ስርዓት ከአገልግሎት ውጭ እያድረገ ነው ብሏል።
የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶችም በሦስቱ ሀገራት የኮቪድ 19 ወረርሽኝ በፍጥነት እየተዛመተ መሆኑን ተከትሎ ነው ከሀገራቱ የሚነሱ መንገደኞች ላይ ክልከላ የጣለቸው።