ዩኒሴፍ፤ በምስራቅ እና ደቡብ አፍሪካ 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ህጻናት የህይወት አድን ህክምና እያገኙ አይደለም ሲል አስጠነቀቀ
በኢትዮጵያ 500 ሺ ገደማ ለከፍተኛ የተመጣጠነ ምግብ እጥረት የተጋለጡ ህጻናት እንዳሉ የዩኒሴፍ መረጃዎች ያመላክታል
ዩኒሴፍ በአፍሪካ የተመጣጠነ ምግብን ለማሳደግ “255 ሚሊዮን ዶላር ያስፈልገኛል” አለ
የመንግስታቱ ድርጅት የህጻናት ፈንድ (ዩኒሴፍ) በአፍሪካ የተመጣጠነ ምግብን ለማሳደግ 255 ሚሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልገው አስታወቀ፡፡
ድርጅቱ ከፍተኛ የገንዘብ መጠን የፈለገበት ምክንያት በ2022 ቅድሚያ ለሚሰጣቸው የምስራቅ እና ደቡብ አፍሪካ ሀገራት የሚሰጠውን የአደጋ ጊዜ የተመጣጠነ ምግብ እርዳታ ለማሳደግ እንደሆነም ነው የገለጸው፡፡
ገንዘቡ በዋናነት ለህጻናት ህክምና እና ህይወት አድን ምግብ ድጋፍ ለማድረግ የሚውል ነው፡፡
ዩኒሴፍ ባወጣው መግለጫ ቢያንስ 1.5 ሚሊዮን ህጻናት በምስራቅ እና ደቡብ አፍሪካ የህይወት አድን ህክምና እያገኙ እንዳልሆነ አስጠንቅቋል።
አጠቃላይ አስቸኳይ እርዳታ የሚያስፈልጋቸው ህጻናት ቁጥር 3.6 ሚሊዮን ገደማ ነው፡፡
- ፋኦ ኢትዮጵያን ጨምሮ በምስራቅ አፍሪካ ሀገራት የተከሰተውን ድርቅ ለመከላከል 138 ሚሊየን ዶላር ድጋፍ አደርጋለሁ አለ
- የአየር ንብረት ለውጥ በምስራቅ አፍሪካ ብቻ በ10 ሚሊየን ሰዎችን ሊያፈናቅል ይችላል- የዓለም ባንክ
የዩኒሴፍ የምስራቅ እና ደቡብ አፍሪካ ዳይሬክተር ሞሃመድ ኤም. ፋል “መዳን እየቻሉ በተመጣጠነ መግብ እጥረት የሚሰቃዩ ህጻናትን ማየት አሳዛኝ ነው” ሲሉም ነበር የችግሩን ጥልቀት የገለጹት፡፡
የኮሮና ወረርሽኝ ተጽዕኖ ለህጻናቱ የሚደረገውን ህክምና የከፋ አድርጎታል እንደ ዳይሬክተሩ ገለጻ፡፡ የገንዘብ እጦትም ተጨማሪ ፈተና ነው፡፡
በአሁኑ ወቅት በምስራቅ እና ደቡብ አፍሪካ የሚስተዋሉ የምግብ እጦት፣ የኢኮኖሚ መበላሸት፣ ወረርሽኝ፣ ጎርፍና ድርቅ እንዲሁም ግጭቶች ችግሩን ይበልጥ እንዲባባስ አድርገዋል እንደ ዩኒሴፍ ገለጻ፡፡
በኢትዮጵያ በተጠናቀቀው የፈረንጆቹ ዓመት ብቻ ለከፍተኛ የተመጣጠነ ምግብ እጥረት የተጋለጡ 500 ሺ ገደማ ህጻናት እንዳሉ የዩኒሴፍ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡