የአየር ንብረት ለውጥ በምስራቅ አፍሪካ ብቻ በ10 ሚሊየን ሰዎችን ሊያፈናቅል ይችላል- የዓለም ባንክ
በአፋጣኝ እርምጃ ካልተወሰደ እስከ 2050 ድረስ ከ38 ሚሊየን በላይ ሰዎች ሊፈናቀሉ እንደሚችል ባንኩ አስታውቋል
ባንኩ በግላስጎው የሚካሄደውን ኮፕ 26 የተመድ ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባዔን አስመልክቶ ሪፖርት አውጥቷል
የአየር ንብረት ለውጥ በቀጣዮቹ ሶስት አስርት ዓመታት ብቻ በምስራቅ አፍሪካ ከሚገኙ ሀገራት በ10 ሚሊየን የሚቆጠሩ ሰዎችን ሊያፈናቅል እንደሚችል የዓለም ባንክ አስታወቀ።
ባንኩ ትናንት ባወጣው መግለጫ የአየር ንብረት ለውጥ ሁኔታ በዚሁ ከቀጠለ እስከ አውሮፓውያኑ 2050 ድረስ ነው ሰዎቹ ከቤት ንብረታቸው ሊፈናቀሉ የሚችሉት።
የአየር ንብረት ለውጥ ሰለባ ሆነው የሚፈናቀሉትም በድርቅ ሳቢያ ሌላ የእርሻ መሬት አሊያም ለየት ያለ ስራ ለመፈለግ ወደ ከተማ እና ሌሎች አካባቢዎች የሚፈልሱ አርሶአደሮች እንዲሁም ንጹህ የመጠጥ ውሃ ፍለጋ ወደ ሌሎች አካባዎች የሚንቀሳቀሱ ሰዎች ይገኙበታል።
ባንኩ ከ4 ቀን በኋላ በግላስጎው እንደሚጀመር የሚጠበቀውን ኮፕ 26 የተመድ የዓለም የአየር ንብረት ለውጥ ጉባዔን አስመልክቶ ባወጣው መረጃ አስታውቋል።
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ 5 የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት ማለትም ኬንያ፣ ታንዛኒያ፣ ሩዋንዳ፣ ኡጋንዳ እና ብሩንዲ በአየር ንብረት ለውጥ ከፉኛ እየተጎዱ መሆኑን ሪፖረቱ ያመለክታል።
በዓለም ባንክ የምስራቅ አፍሪካ ቀጠና ምክትል ፐሬዝዳንት ሃፌዝ ግሃኔም፤ በአየር ንብረት ለውጥ ዙሪያ መጠነ ሰፊ እርምጃ በአፋጣኝ ካልተወሰደ እስከ 2050 ድረስ 38 ነጥብ 5 ሚሊየን ሰዎች ሊፈናቀሉ ይችላሉ ብለዋል።
የካርቦን ልቀት መቀነስን ጨምሮ ሌሎች የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል የሚረዱ እርምጃዎችን በአፋጣኝ መውሰድ ከተቻለ የተፈናቃዮችን ቁጥር በ30 በመቶ መቀነስ እንደሚቻልም አስታውቀዋል።