በአውሮፓ ከዩክሬናዊያን ውጪ አንድ ሚሊዮን ስደተኛ ጠያቂዎች መኖራቸው ተገለጸ
ከስደተኛ ጠያቂዎች መካከል የቱርክ፣ ሶሪያ፣ ቬንዙዌላ፣ አፍጋኒስታን እና ኮሎምቢያ ዋነኞቹ ናቸው ተብሏል
ሀንጋሪ እና ፖላንድ አስቀድመው ስደተኞችን እንደማይቀበሉ አስታውቀዋል
በአውሮፓ ከዩክሬናዊያን ውጪ አንድ ሚሊዮን ስደተኛ ጠያቂዎች መኖራቸው ተገለጸ።
አውሮፓ ከመቼውም ጊዜ በላይ ከፍተኛ ቁጥር ያለው የስደተኝነት ጥያቄዎች እንደቀረቡለት አስታውቋል።
ይህን ተከትሎ የአውሮፓ ሀገራት መሪዎች በስደተኞች ቅበላ ዙሪያ መስማማት እንዳልቻሉ ዶቸቪሌ ዘግቧል።
የአውሮፓ ህብረት የስደተኝነት ጥያቄ ያቀረቡ ዜጎችን ለመርዳት አዲስ ፖሊሲ በማዘጋጀት ላይ መሆኑን ቢያስታውቅም ሀንጋሪ እና ፖላንድ ግን አስቀድመው አንድም ስደተኛ የመቀበል ፍላጎት እንደሌላቸው አስታውቀዋል።
ጀርመን 244 ሺህ ስደተኞችን ለመቀበል ፈቃደኛ በመሆን ቀዳሚ ሀገር ስትሆን ፈረንሳይ፣ ስፔን፣ ኦስትሪያ እና ጣልያን በአንጻራዊነት ብዙ ስደተኞችን ለመቀበል ፈቃድ ያሳዩ ሀገራት ናቸው።
ይሁንና ዩክሬንን ጨምሮ ተጨማሪ አራት ሚሊዮን ስደተኞች በአውሮፓ ሀገራት ተጠልለው በመጠባበቅ ላይ ናቸው መባሉ ህብረቱን ፈተና ውስጥ እንደከተተውም ተገልጿል።
አውሮፓ ህብረት ባወጣው አዲሱ እቅድ መሰረት ሀገራት ስደተኞችን እንዲቀበሉ አልያም በተጣለባቸው ኮታ መሰረት በአንድ ስደተኛ 21 ሺህ ዶላር እንዲከፍሉ ጠይቋል።
አሁንም ተጨማሪ ስደተኞች ወደ አውሮፓ ሀገራት በመግባት ላይ እና ለመግባት ጥረት ላይ መሆናቸው አውሮፓ በተጨማሪ ስደተኞች ልትጥለቀለቅ እንደምትችል ተሰግቷል።