ባለፉት 3 ዓመታት ከ18 ሺ የሚልቁ ስደተኛ ህጻናት አውሮፓ ከደረሱ በኋላ ጠፍተዋል ተባለ
አብዛኞቹ ጣሊያንን ጨምሮ በሜዲትራኒያን ባህር ዳርቻ አቅራቢያ በሚገኙ የአውሮፓ ሃገራት መጥፋታቸው ነው የተነገረው
ህጻናቱ ወሲብን ጨምሮ ለተለያዩ ብዝበዛዎች እንዳይዳረጉ ተሰግቷል
ከጎርጎሮሳውያኑ 2018 ጀምሮ ከ18 ሺ የሚልቁ ስደተኛ ህጻናት አውሮፓ ከደረሱ በኋላ መጥፋታቸው ተነገረ፡፡
‘ሎስት ኢን ዩሮፕ’ በተባለ ፕሮጀክት ተካሂዷል የተባለው ጥናት ህጻናቱ ለህገወጥ የሰው እና የአደንዛዥ እጽ አዘዋዋሪዎች ብዝበዛ እንዳይጋለጡ አሳስቧል፡፡
ጥናቱ 18 ሺ 292 ስደተኛ ህጻናት አውሮፓ ከደረሱ በኋላ ጠፍተዋል ነው የሚለው፡፡
ሆኖም ጥናቱ ፈረንሳይን የመሳሰሉ የበርካታ ስደተኞች መዳረሻ ሃገራትን መረጃ አላካተተም፡፡
የፍልሰተኞች አስተዳደር ህጓን በአዲስ መልክ ያሻሻለችውን እንግሊዝንም አላካተተም፡፡
ይህም ቁጥሩ ከዚህም በላይ ሊያሻቅብ እንደሚችል ማሳያ ተደርጎ ተወስዷል፡፡
አብዛኞቹ ህጻናት የጠፉት በሜዲትራኒያን ባህር ዳርቻ አቅራቢያ በሚገኙ ጣሊያንን መሰል የአውሮፓ ሃገራት ነው፡፡
በጣሊያን 6 ሺ፣ በግሪክ 2 ሺ እና በስፔን 1 ሺ 900 ስደተኛ ህጻናት ሳይጠፉ እንዳልቀረ ጥናቱ አመልክቷል፡፡
በኔዘርላንድ 2 ሺ 600 ገደማ ህጻናት ሳይጠፉ እንዳልቀረ የሚጠቁምም ሲሆን በቤልጂዬም የጠፉት ከ1 ሺ ይልቃሉ ይላል፡፡
የህጻናቱ መጥፋት ከአየርላንድ እስከ ማልታ ባሉ የአውሮፓ ሃገራት ሪፖርት መደረጉንም ነው የዘ ናሽናል ዘገባ ያመለከተው፡፡
የህጻናቱ ተጋላጭነት የሚያይለው ከወላጆቻቸው ተነጥለው ሲጓዙ እንደሆነም ተጠቁሟል፡፡
አል-ሆል በተሰኘው የሶሪያ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ ከ30 ሺ በላይ ህጻናት ይገኛሉም ነው የተባለው፡፡