የኡሁሩ ኬንያታ መንግስት ጣቢያዎቹን በ14 ቀናት ውስጥ እንዲዘጋ ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት ከፍተኛ የስደተኞች ኮሚሽን ማሳሰቢያ ሰጥቷል ተብሏል
የመንግስት ካቢኔ ዋና ጸሃፊው ዶ/ር ፍሬድ ማቲያንጌ ኬንያ ጣቢያዎቹን አስመልክቶ በሰጡት መግለጫ ድርጅቱ በ14 ቀናት ውስጥ እንዲዘጋ ማስጠንቀቂያ ማስተላለፏን ዘ ስታር የተሰኘው ጋዜጣ ዘግቧል።
ኬኒያ ከዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰችው መነሻቸውን ከስደተኞች መጠለያዎች ያደረጉ የሽብር ጥቃቶች ስጋት ስላለ መሆኑን ዘገባው ጠቁሟል።
የዳዳብ እና ካኩማ ስደተኛ መጠለያዎች የተሻለ ደህንነት ፍለጋ በሚል ከአገራቸው የተሰደዱ ሶማሊያዊያን መጠለያዎች ናቸው።ኬንያ በተደጋጋሚ እነዚህን መጠለያ ጣቢያዎች የብሄራዊ ደህንነት ስጋት ምንጮች በመሆናቸው እዘጋለሁ ስትል ዓመታትን ያስቆጠረች ቢሆንም ወደ ተግባር ሳትገባ ቆይታለች።
ይሁንና እዘጋለሁ የሚለው ውሳኔ ኬንያ እና ሱማሊያ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን ባቋረጡበት ወቅት መሆኑ ኬንያ ውሳኔውን እንዳለችው ልትተገብረው ትችላለች ተብሏል።
በአሁኑ ወቅት በዳዳብ እና ካኩማ ስደተኞች መጠለያ ጣቢያዎች ውስጥ ከ400 ሺህ በላይ ሶማሊያዊያን በስደተኝነት ተጠልለው ይገኛሉ።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ከፍተኛ የስደተኞች ኮሚሽን ከኬንያ መንግስት የተሰጠው ማሳሰቢያ እንደደረሰው ገልጿል።
ይሁንና ወቅቱ የኮሮና ቫይረስ የተስፋፋበት ወቅት በመሆኑ በአጭር ጊዜ ውስጥ ስደተኛ ጣቢያዎቹን ለመዝጋት አስቸጋሪ ሊሆን እንደሚችል ገልጾ ቀጣይ ድርድሮችን ከኬንያ መንግስት ጋር እንደሚያደርግ ኮሚሽኑ አስታውቋል።
ኬንያ የዳዳብ እና ካኩማ ስደተኞች መጠለያ ጣቢያዎችን እዘጋለሁ ማለት የጀመረችው በእነደ ጎርጎሮሲያን ዘመን አቆጣጠር ከ2016 ዓመት በጋሪሳ ዩንቨርሲቲ በመቶዎች የሚቆጠሩ ተማሪዎች ከተገደሉባት በኋላ ነበር።