የ28 ዓመት አልጀሪያዊ ወጣት ያሸነፈው የሎተሪ ሽልማት መሆኑ ችግር ውስጥ ከቶታል
ስሙ እንዳይጠቀስ የፈለገ አንድ የ28 ዓመት አልጀሪያዊ ወጣት የተሻለ ህይወት ፍለጋ ነበር ወደ አውሮፓዊቷ ሀገር ቤልጂየም ያመራው።
በቤልጂየሟ ብሩዥ ከተማ በጥገኝነት ይኖር የነበረው ይህ ወጣት ወጣት የእድል በሯ አይታወቅም ሊወጣልኝ ይችላል 250 ሺህ ዩሮ የሚያሸልም የሎተሪ እጣ ቁጥር ይገዛል።
አልጀሪያዊው ስደተኛ ወጣትም 250 ሺህ ዩሮ ወይም 14 ሚሊየን ብር የሚያሸልመው ሎተሪ እጣ ማሸነፉን ይሰማል።
ይሁንና ይህ አልጀሪያዊ ወጣት ያሸነፈው የሎተሪ ሽልማት ገንዘብ መጠን ብዙ በመሆኑ በካሽ እንዲከፈል የሀገሪቱ ህግ የሚከለክል መሆኑ ችግር ውስጥ ከቶታል።
ስደተኛው በቤልጂየም ሲኖር ህገዊ የመኖሪያ ፈቃድ ስለሌለው እና እጁ ላይ ያለው መረጃ የባንክ ሂሳብ የሚያስከፍተው ባለመሆኑ በሎተሪ ያሸነፈውን ገንዘብ መቀበል አለመቻሉን ኤኤፍፒ ዘገባ ያስረዳል።
ገንዘቡን ከሎተሪ ድርጅቱ ለመቀበል የተቸገረው ይህ እድለኛ ስደተኛ ወጣት ህጋዊ የመኖሪያ ፈቃድ ባለው ጓደኛው በኩል ለመቀበል ጥረት ቢያደርግም ፖሊስ በማጭበርበር ወንጀል ጠርጥሯቸው አስሯቸዋል።
የሚያደርገው የቸገረው ይህ ወጣትም ጠበቃ ቀጥሮ ክርክር የጀመረ ሲሆን ማንነቱን የሚያስረዱ መረጃዎችን ከእናት አገሩ አልጀሪያ ቢያመጣ የተሻለ እንደሆነ ተነግሮታል።
ጉዳዩ አሁን ላይ ወደ ፍርድ ቤት አምርቶ ክርክር እየተካሄደበት ሲሆን እድለኛው ስደተኛ የመኖሪያ ፈቃድ ስለሌለው ወደ አልጀሪያ በግዴታ ሊላክ ይችላል እየተባለ ሲሆን በርካቶች ግን ፖሊስ ይሄንን እንዳያደርግ በመማጸን ላይ ናቸው።
እድለኛው ስደተኛ ከአራት ወር በፊት ነበር ከአገሩ አልጀሪያ በህገወጥ መንገድ በጀልባ ተጉዞ ስፔን ከገባ በኋላ በእግሩ ከፈረንሳይ ወደ ቤልጂየም መግባቱ ተገልጿል።
ስደተኛው ወደ እንግሊዝ የመግባት ፍላጎት ቢኖረውም በተለያዩ ምክንያቶች በቤልጂየም ሊቆይ ችሏልም ተብሏል።