በ2021 የ10 የእግር ኳስ ሜዳ ያህል ስፋት ያለው ደን በየደቂቃው ይወድም ነበር ተባለ
ከ11 ሚሊዮን ሄክታር በላይ የደን ይዞታ መውደሙ ተነግሯል
ከወደመው ውስጥ 40 በመቶ ያህሉ በብራዚል የወደመ ነው
በፈረንጆቹ 2021 ቢያንስ በትንሹ የ10 የእግር ኳስ ሜዳ ያህል ስፋት ያለው ደን በየደቂቃው ይወድም ነበር ተባለ፡፡
ደኑ ቃጠሎን ጨምሮ በተለያዩ መንገዶች ይወድም እንደነበር በግሎባል ፎረስት ወች የተደረገው ጥናት አመልክቷል፡፡
በተጠቀሰው ዓመት ውስጥ 11 ነጥብ 1 ሚሊዮን ሄክታር የደን ሽፋን መውደሙንም ነው ጥናቱ ያመለከተው፡፡ ከወደሙት የደኑ አካል የሆኑ ዛፎች ውስጥ 3 ነጥብ 75 ሚሊዮን ሄክታር ያህሉ ዕድሜ ጠገብ ዛፎች ናቸው፡፡
"በየደቂቃው 10 የእግር ኳስ ሜዳ ያህል ደን ዓመቱን ሙሉ ሲወድም ነበር"ም ብለዋል አጥኚዎቹ፡፡
በዚህም የህንድን ዓመታዊ የበካይ ጋዝ ልቀት ያህል ጋዝ ወደ ከባቢ አየር ይገባ እንደነበርም ገልጸዋል፡፡
የውድመቱ 40 በመቶ በብራዚል የደረሰ ነው፡፡ የአማዞን አካል ከሆነው የብራዚል ደን 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሄክታር ያህሉ ተጨፍጭፏል ወይም ወድሟል፡፡
ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ 500 ሺ ሄክታር እንዲሁም ቦልቪያ 300 ሺ ሄክታር ያህል ደን ወድሞባቸዋል፡፡
የደኖች የውድመቱ መጠን ከባለፈው ተመሳሳይ ዓመት ጋር ሲነጻጸር ቅናሽ አሳይቷል፡፡ ሆኖም ውድመቱ ቀጥሏል፡፡
እምብዛም የከፋ ውድመት አጋጥሞ በማይታወቅበት በሩሲያ አካባቢ እንኳ 6 ነጥብ 5ሚሊዮን ሄክታር ደን ወድሟል፡፡