በህልም መንስኤዎችና ፍቺዎች ዙሪያ የሚቀርቡ መረጃዎች ማከራከራቸውን ቀጥለዋል
የሰው ልጅ በህይወት ዘመኑ ሲሶውን በእንቅልፍ እንደሚያሳልፍ ጥናቶች ያሳያሉ።
እያንዳንዱ ሰው በየቀኑ ከ15 እስከ 40 ደቂቃ የሚረዝም ህይል ያያል።
እስከ ህይወቱ ህልፈት ደረስም በአማካይ 6 አመት ያህል ርዝማኔ ያለው ህልም እንደሚያይም ነው የሄልዝ ላይን መረጃ የሚያሳየው።
ህልም አይተን ስንነቃ በ5 ደቂቃ ውስጥ 50 ከመቶውን፤ በ10 ደቂቃ ውስጥ ደግሞ 90 በመቶውን የተመለከትነውን ነገር እንረሳዋለን።
የአብዛኞቻችን ውሎ ወከባና ጭንቀት ስለሚበዛውም ከሚያስደስቱ ህልሞች ይልቅ ጭንቀት የሚጨምሩ ህልሞች እንደሚደጋገሙም ነው ባለሙያዎች የሚናገሩት።
ህልም ከቆዩ ትውስታዎቻችን በየቀኑ ከሚገጥሙን ጉዳዮች ጋር የተዛመደ እንደመሆኑ የምናየው ህልም ጉራማይሌ የመሆኑ ነገር አጠያያቂ አይደለም።
ለዚህም ነው ለእያንዳድንዱ ሰው ህልም ሳይንሳዊ ፍቺ መስጠት አይቻልም የሚባለው።
አንዳንዶቹ ህልሞች ግን የመመሳሰል ባህሪ እንዳላቸው የእንቅልፍና ተያያዥ ጉዳዮች ተመራማሪዎች የሚናገሩት።
ዶክተር ዴሲ ሜይ ጎግል ላይ በተደጋጋሚ ትርጓሜያቸው የሚጠየቁ 10 የህልም አይነቶችን ወርሃዊ አሃዞችን ጠቅሰው ይፋ አድርገዋል።
ሰዎች በተደጋጋሚ ፍቺያቸውን የሚጠይቋቸው የህልም አይነቶች
1. የጥርስ መውለቅ - 22,200
2. ሸረሪት - 5,400
3. የሚያሳድድ ሰው - 2,400
4. የጸጉር መበጣጠስ - 2,000
5. መውደቅ - 1,900
6. የቀድሞ ፍቅረኛ - 1,900
7. መብረር - 1,800
8. ሞት - 1,600
9. ማጭበርበር - 1,300
10. ፍቅረኛ ሲወሰልት - 1,200
ዶክተር ዴሲ ከላይ የዘረዘሯቸውን የተለመዱ የህልም አይነቶች ፍቺም ይህ ሊሆን ይችላል የሚል አስተያየታቸውን አክለዋል።
ጥርስ ሲወልቅ በህልም ማየት “ከቤተሰብ፣ ከፍቅር አጋራችን ወይም ከሌላ ጉዳይ ጋር በተገናኘ የምናጣው ነገር እንዳለ መጨነቃችን እና ከዚህ ጋር የተያያዘ ነገር ሊገጥመን እንደሚችል ያሳያል” ይላሉ ዶክተር ዴሲ ሜይ።
“እድሜያችን እየጨመረ፤ ውበታችንም እየረገፈ ነው ብለን ስናምን ደግሞ የጸጉር መነቃቀል ህልም ልናይ እንችላለን” ነው የሚሉት ተመራማሪዋ።
በህይወታችን ልናስወግደው የምንፈልገውን ችግር ከመቅረፍ ይልቅ መሸሽን ስንመርጥ ደግሞ በህልማችን ሰዎች ሲያባርሩን ልንመለከት እንችላለን፤ ሰለሆነም የሚያሳድደን ነገር በእውን ሳይዘን ልንፈታው ግድ ነው ብለዋል ዶክተር ዴሲ።
ህልም እንዴት ይከሰታል? በሚለው ዙሪያ የተለያዩ መላምቶች መጠቀሳቸውን ቢቀጥሉም አሁንም ድረስ ክርክሩ ቀጥሏል።
በተለይ በህልም ፍቺ ዙሪያ የሚወጡ ጥናቶች ከትችት አያመልጡም።